Sunday, July 1, 2012

አጀንዳችን አንድ ነው - ሃይማኖታችን እና ቤተ ክርስቲያናችን ብቻ!!!!!!


To Read, Print & share, click HERE (PDF).
(ደጀ ሰላም፤ ሜይ 13/ 2011)፦  ላለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት በተደጋጋሚ ስናሳስብ እንደቆየነው ቤተ ክርስቲያናችንን ከፊት ከኋላ፣ ከግራ ከቀኝ እና ከውስጥ ጠፍንገው የያዟት ችግሮች የበለጠ እየተገለጡ፣ ፈተና የሆኑባት ግለሰቦችም የበለጠ እየታወቁ፣ በሕዝቡ ዘንድ ይፈጥሩ የነበሩትም ብዥታና ግርታ የበለጠ እየጠራ በመምጣት ላይ ይገኛል። ቤተ ክርስቲያን በውስጥም በውጪም ብዙ ፈተናዎች የተደቀኑባት ቢሆንም ከውስጥ ተቀምጠው፣ እንጀራዋን እየበሉ ተረካዛቸውን የሚያነሱባት ግን ፋታ የሚሰጧት አልሆኑም። እነዚህን የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች እና የተሰጣቸውን አደራ አራካሾች ሳናሰልስ ተግባራቸውን በመቃወምና ለምእመኑም ለማሳወቅ በመጣር ላይ እንገኛለን። እነዚህ የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች የተንጠለጠሉበት ካስማ ደግሞ ሁለት ነው። አንደኛው ሙስና፣ ሁለተኛው ኑፋቄ። ደጀ ሰላምም በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የሰፈነውን ሙስና ትቃወማለች፣ ሰርገው የገቡትን መናፍቃን እና የሚዘሩትን ኑፋቄ ትጸየፋለች። ምን ማለታችን እንደሆነ እናብራራው።

በየትኛውም መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ውስጥ ይብዛም ይነሥም ሙስና መኖሩ ይታወቃል። በአገራችን ደረጃ ከተመለከትነው በየደራጀው ሙስና እንዳለ በዚህም ምክንያት ከሥልጣናቸው የተባረሩ ሰዎች መኖራቸውን በመገናኛ ብዙሃን እንሰማለን፣ እንመለከታለን፣ እናነባለን። የሙስናው አየር ከነፈሰባቸው ተቋማት መካከል ደግሞ ግንባር ቀደምነቱን ሊይዝ የሚገባው የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ነው። ስለዚህ ጉዳይ በተደጋጋሚ የጻፍን በመሆኑ አንመለስበትም። በጠቅላላ ለማስቀመጥ ግን ያለ አግባብ በሥልጣን በመባለግ፣ እጅ መንሻ ወይም ጉቦ በመቀበል፣ ከምእመናን የተሰበሰውን ገንዘብ እና ቁሳቁስ ለግል ጥቅም በማዋል፣ የትኛውንም ጉዳይ ለማስፈጸምም ሆነ ተመሳሳይ ተግባር ለማከናወን ጉቦን እንደ መፍትሔ መጠቀም እጅግ በጣም ሰልጥኗል። ይህ ብልሹ አሠራር በጊዜው እንዳይገታ ደግሞ የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር ፍላጎትም ችሎታም የለውም።
ሙስና በምድራዊ ሕግ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊውም ሕግ የተጠላ እና የተከለከለ ቢሆንም ሃይማኖታዊውን ሕግ የሚያውቁ እና የመንፈስ ልዕልና ኖሯቸው ሌላውን በትምህርታቸው ተግሳጽ፣ በቃላቸው ምክር ሊያቀኑ የሚገባቸው ሰዎች እና ይህንን ልታደርግ ይገባት የነበረች ተቋም የዚህ መፈብረኪያ ስትሆን በሽታው መድሃኒት ሊያገኝ አይችልም። የበሽታ ማጥፊያ መድሃኒቶችን እንደሚላመዱ የበሽታ አምጪ ሕዋሶች፣ ቃለ እግዚአብሔር እና ኢትዮጵያዊ ሥነ ምግባርን በመጣስና በመደምሰስ ዓይን ያወጣ ዝርፊያ በማጧጧፍ ላይ ናቸው።
ሠራተኛ መበደል፣ ንብረት ማባከን፣ ጉቦ መቀበል በዚህም ደግሞ የራስን ንብረት ማከማቸት ለካህን እና ለክህነት የማይገባ ድርጊት መፈጸም የአደባባይ ምሥጢር ሆኗል። ይህም ከርዕሰ ቤተ ክርስቲያኑ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ የሚታወቅ ቢሆንም እርሳቸውም የችግሩ አካል በመሆን ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ ውድቀት አፋፍ ከመግፋት ውጪ ራሳቸውም ድርጊቱን ተጸይፈው ሌላውን ሊወቅሱ አልቻሉም። በዙሪያቸው በሰበሰቡት የቤተ ዘመድ ጉባኤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሲያስነቅፉ እና ሲያዋርዱ ዓመታት አስቆጥረዋል። አሁንም ቀጥለዋል።
ይህም ሳያንስ አሁን ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱን በተሐድሶ የኑፋቄ ትምህርት ለማበላሸት ለሚፈልጉ ሰዎች ነገሮችን በማመቻቸት ችግሩን የበለጠ አስፈሪና አስቸጋሪ አድርገውታል። ገንዘብ ቢዘረፍ በገዘንዘብ ይተካል። ንብረት ቢወድም በንብረት ይካካሳል። እምነት ከተበላሸ ግን በምን ይስተካከላል?
ኢትዮጵያ ሕብረ-እምነት ያላት አገር መሆኗን እናምናለን። ኢትዮጵያ የአንድ እምነት ብቻ የሚል ጅል አስተሳሰብ የለንም። ሁሉም የየራሱን እምነት አክብሮ እስከኖረ ድረስ አንድ ሰው ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት የተለየ አስተሳሰብ ስላራመደ ችግር ይገጥመው ዘንድ አንመኝም።፡ ለዚህም ነው ጥቂት አክራሪ ሙስሊሞች በጅማ አካባቢ በፕሮቴስታንቶች ላይ ያደረሱትን አደጋ አምርረን የተቃወምነው። ነገ በሙስሊም ወገኖቻችን ላይ ተመሳሳይ ችግር ቢደቀን አብረናቸው ከመቃወም ወደ ኋላ አንልም። ነገር ግን የሌላ እምነት፣ ቡድን እና ግለሰብ በእምነት መፈጸሚያ ቦታችን እና በመዋቅራችን በድብቅ ሰርጎ በመግባት የሚፈጽመውን ተንኮል አጥብቀን እንቃወማለን። ተሐድሷውያን ፍፁም የለየላቸው ፕሮቴስታንቶች ሆነው ሳለ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የሚፈጽሙትን ደባ አምርረን የምንቃወመው ያለ እምነታቸው እና ያለ ቤታቸው በመግባታቸው ነው። ጦማሪው ዳንኤል ክብረት በአንድ ጽሑፉ እንዳለው “ሤራ፣ ተንኮል፣ ስለላ፣ ማጭበርበር እና እምነት ምን አገናኛቸው?” በቤታችንስ ማን አስገባቸው? እስካልወጡ ድረስም እንቅልፍ አይኖረንም እንላቸዋለን። ይህ ደግሞ የደጀ ሰላም ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኦርቶዶክሳውያን አቋም እና እምነት ነው።
ቤተ ክርስቲያናችንን ፈተና የሆኗት እነዚህ ሁለት ቡድኖች (ሙሰኞች እና ተሐድሶዎች) ዓላማቸውን ለማስፈጸም የጋራ ግንባር በመፍጠር እንደሚሠሩ ከዕለት ዕለት ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ግልጽ ሆነ ያልነው ለእኛ ሳይሆን የችግሩን መኖር ይጠራጠሩ ለነበሩ አካላት ነው። ሙሰኞቹ ገንዘብ እስካገኙ ድረስ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከመሸጥ አይመለሱም። ተሐድሶዎቹ ደግሞ ዓላማቸውን የሚያስፈጽምላቸው ሰው እስካገኙ ድረስ ገንዘብ ለመስጠት እና ለመተባበር ወደኋላ አይሉም። ለዚህም ነው ትናንት የተጣሉ ይመስሉን የነበሩ ሰዎች ዛሬ ግን እጅግ የሚዋደዱ መስለው በሕብረት ቆመው የምናያቸው። እነዚህ ሁለት ቡድኖች ደግሞ ዓላማቸውን የሚያሰናክልባቸው የመሰላቸውን ማንኛውንም አካል ከማጥፋት ወደኋላ አይሉም። አላሉምም። ሁለቱም ወገኖች ዓላማቸውን ለማስፈጸሚያነት፣ የሚቃወማቸውን ለማጥቂያነት ለመጠቀም የሚፈልጉት መንግሥትን እና ያለውን አስተዳደራዊ መዋቅሩን ነው። መንግሥት ለእነዚህ ወገኖች በመጠቀሚያነት ይውላል የሚል እምነት ባይኖረንም ሙከራቸው ግን እንዳለ እርግጠኞች ነን። ይህ ደግሞ ጥንትም የነበረ እንጂ አዲስ የመጣ ዘዴ አይደለም።
ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚያስተምረን አይሁድ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከከሰሱባቸው ክሶች መካከል አንደኛው ከሮማውያን ገዢዎቻቸው ጋር ለማጋጨት የተጠቀሙበት “ራሱን የአይሁድ ንጉሥ  ነኝ ይላል” የሚለው ፖለቲካዊ ክስ ነው። ንጉሥ በንጉስነቱ፣ ወንድ ልጅ በሚስቱ፣ እግዚአብሔር በመለኮቱ ሲመጡበት … እንደሚባለው ጌታን ከሮም ቤተ መንግሥት ጋር በማጋጨት ሊያሰቅሉት ሞክረዋል። ይህ በጌታችን ላይ የተደረገው ነገር በየዘመኑ በተለያየ መልክና ቅርጽ ሲፈጸም ኖሯል።
ሌላውን ትተን በተለያየ ዘመን በአገራችን እንኳን የነበረውን ሁኔታ ብንመለከት እበላ ባይ ደባትር በነገረ ሰሪነት ወደ ነገሥታቱ በመቅረብ ንፁሐን እና ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ላይ አደጋ ሲያደርሱ ኖረዋል። “እገሌ እና እገሌ በሥልጣንህ መጥተውብሃል” በሚለው ክፉ ወሬያቸው የብዙዎችን ደም አስፈስሰዋል። ብዙዎችንም በግዞት እንዲጣሉ፣ በእግር ብረት እንዲታሰሩ፣ በብቸኝነት እንዲንከራተቱ፣ አገር ጥለው እንዲሰደዱ አስደርገዋል። ለአብነት የደብረ ሊባኖሱን ቅዱሱን የአባ ፊሊጶስን ግዞት እና ግርፋት፣ የጋስጫውን የአባ ጊዮርጊስን ግዞት፣ የነአባ በጸሎተ ሚካኤልን መከራ መጥቀስ ይቻላል።
እነዚህ ነገሥታት በቅዱሳኑ ላይ መከራ ያጸኑባቸው በነገረ ሠሪዎቹ ተታለው እንጂ ራሳቸው ክፉዎች ነገሥታት ስለነበሩ አልነበረም። በሌሎች መልካም ተግባሮቻቸው የተመሰገኑ መሆናቸውን ታሪክ ይነግረናል። ይሁን እንጂ ቤተ ክህነቱን መጠጊያ የሚያደርጉ ተንኮለኞች በሚፈጽሟቸው በደሎች ብዙዎች የመከራው ቀንበር ይወድቅባቸዋል። በዚህ ዘመንም የኢሕአዴግ አባላት ነን፣ በመንግሥት ዘንድ ሞገስ አለን፣ ሥልጣን አለን፣ የአገር ልጅነት እና አምቻ ጋብቻ አለን የሚሉ ሰዎች ብዙ መልካም ሰዎች ላይ የመከራ ቀንበር በማስጫን ላይ ናቸው።
እነዚህ በክህነታቸው በቤተ ክህነት፣ በፓርቲ አባልነታቸው ከመንግሥት የተጠጉ ጥቅመኞች ቤተ ክርስቲያኒቱን እየጎዱ ነው፤ የመንግሥትንም ስም እያስጠፉ ነው። ራሳቸውን የመንግሥት  ብቸኛ ወገንና ልጅ፣ ሌላውን ባዳና የእንጀራ ልጅ አድርገው በማቅረብ በአንድ አገር ሁለት ዜጋ ያለ እያስመሰሉ ነው። የመንግሥት መንግሥትነቱ ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ለእኛም ነው። በሕግ ፊት ሁላችንም እኩል ነን። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች በሚፈጽሙት ወንጀል ተያቂ ባለመሆናቸው በብዙው ምእመን ዘንድ ከሕግ በላይ የሆኑ አስመስሏቸዋል።
በአገራችን ልማት እንዲመጣ እንመኛለን። አመጽን፣ ብጥብጥን፣ በእምነቶች መካከል ሊከሰት የሚችልን አለመቻቻል እንቃወማለን። ይህም ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያናችን ያለውን ሙስና እና ሰርጎ የገባ ተሐድሷዊ የመናፍቃን ተንኮልም እንቃወማለን። እነዚህን ሙሰኞች እና ተሐድሶዎች የምንቃወማቸው ባላቸው የፖለቲካ አቋም ሳይሆን በእምነታችን ላይ በሚፈጽሙት ወንጀል ነው። አጀንዳችን አንድ እና አንድ ነው፦ እነዚህን የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች መቃወም።

No comments:

Post a Comment