Wednesday, June 20, 2012

ኢህአዴግ “በአዲስ ራእይ” መጽሄት ምን እያለ ነው?



  • በተመሳሳይ አንዳንድ ኦርቶዶክስ ክርስትያኖች ሌላው ቀርቶ የተለየ አመለካከት ያላቸው ክርስትያኖችንም ቢሆን የሚከተሉትን እምነት ክርስትና አይደለም ብለው ከማመን አልፈው ፤ እነዚህ ተለየ አመለካከት ያላቸው ዜጎች እምነታቸውን በነጻነት እንዳያራምዱ በተለያየ ሽፋን ማፈን ይከጅላቸዋል፡፡
  • ኢትዮጵያ የክርስትያነ ደሴት ናት ከሚል ቅዥት ባለፈ አንድ “ሀገር አንድ ሃይማኖት” የሚል መፈክር ደረታቸው ላይ ለጥፈው ለመሄድ እንኳን ሀፍረት የማይሰማቸው ሆነው በአደባባይ ይታያሉ
  • ወሃቢያን ወይም ሌላው የመከተል የማህበረ ቅዱሳንን ወይም ሌላ አተያይ የመያዝ መብት የዜጎች ነው 
  • ህዝብ እንዲያገለግል የተቀመጠ ኃላፊና ሰራተኛ በራሱ እምነት ምስሎች አጨመላልቆየምናይበት ሁኔታ መንግስትና ሃይማኖትን ለመለየት የተቀመጠውን ድንጋጌ በቀጥታ በመጻረር በመሆኑ መወገዝ መወገድ የሚገባው ነው፡
  • በክርስትና ውስጥም በአንድ ወይም በሌላ መልኩ በተለይ ከማህበረ ቅዱሳንም የተወሰኑ ከመሰረታዊ የእምነቱ አስተምህሮ ፈንጠር ያሉ .........
  • እነዚህ ፅንፈኞች በርካታ ንጹሀን ዜጎችን አሳስተው በማነሳሳትና አንዱ በሌላው  ለመዝመት የተዘጋጁ በማስመሰል የፍጥጫ ድባብ እንዲነግስ የሚሰሩ ናቸው

(አንድ አድርገን ሰኔ 12 /2004ዓ.ም)፡-PART 1
አዲስ ራዕይ በየሁለት ወሩ በአማርኛ ቋንቋ እየተዘጋጀች በኢኮኖሚያዊ ፤ ፖለቲካዊ ፤ ማህበራዊ ፤ ዓለም ዓቀፋዊና ፤ ድርጅታዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራያና ትንታኔ ይዛ የምትቀርብ የኢህአዴግ የትንታኔ መጽሄት ነች፡፡ የዚች መጽሄት አዘጋጅ “የኢህአዴግ ህዝብ ግንኙነት ክፍል” ሲሆን አሳታሚው ደግሞ “ኢህአዴግ” መሆኑን የመጽሄቷ የፊት ገጽ ላይ የሰፈረው ጽሁፍ ይናገራል ፡፡ 

እንደ መረጃዎች ይች መጽሄት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚነሱ ሀሳቦች ላይ ታጠነጥናለች አንዳንዴም ጸሀፊው እርሳቸው ናቸው የሚባልም ወሬ አለ፤ አቶ መለስም ጻፉት ሌሎች አባላት ታትሞ ከወጣ የድርጅታቸው አቋም  ነው አመለካከታቸው እሳቤያቸውንና ተግባራቸውን ከሞላ ጎደል የምታዩባት ክፍል ነች ፤  ይህች መጽሄት ተደናሽነቷ ለኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ፤ መንግስት በሹመት ያስቀመጣቸው በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ኃላፊዎች ፤ ከህዋስ ደረጃ ከፍ ያሉ አባላት ብቻ  በመሆኑ እንዲህው በቀላሉ በማንም እጅ ላይ የመታየት እድሏ እጅጉን አናሳ ነው ፤  እዚች መጽሄት ላይ የሰፈረው ሀሳብን መሰረት በማድረግ የኢህአዴግ ከወረዳ አንስቶ እስከ ሚኒስትርነት ያስቀመጣቸው ሰዎች በድርጅታዊ ጉባኤ እንደሚነጋገሩበትና ይዘቷን የሚፈትሹበት ፤ ጽሁፉን ላነበቡትም ሆነ ላላነበቡትም አባላት የመንስትን አቋም የሚያውቁበት መድረክ በየጊዜው እንዳላቸው ውስጥ አዋቂዎች ተንፍሰውልናል፡፡ አዲስ ራእይ በ2ኛ ዓመት ቅጽ 3 ግንቦት-ሰኔ 2004 ዓ.ም ለመዳሰስ የተፈለገው ዋናው ጉዳይ በፖለቲካ አምዷ በአሁኑ ሰዓት ሀገሪቱ የእግር እሳት የሆነባትን የሀይማኖት ጉዳይ ነው ፤ ኢህአዴግ በዚች 70 ገጽ በማትሞላ መጽሄት በአሁኑ ሰዓት ያለውን የሀይማኖት ችግር መሰረት በማድረግ 41 ገጹን በሚሸፍን መልኩ መተንፈስ ችሏል ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ከሰጡት የሰዓታት ትንታኔ ጠለቅ ባለ መልኩ ነገሮችን በስፋትና በጥልቀት በደፈረሰ አይኑ ተመልክቶ ሀሳቡን ማቀመጥ ችሏል ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስተ ተዋህዶ ቤተክርስትያን “አንዳንድ አማኞች” በማለት በግልጽ ያለውን እና የያዘውን አቋም ሲያንጸባርቅ አስተውለናል ፤

አክራሪነትን ከህገ መንግስቱ አንጻር የተመለከተ መስሎት የማይመለከተን እኛንም በደንብ አድርጎ ወርፎናል ፤ በየቢሮ የሚለጠፉ የቅዱሳን ስዕላትንና የመጽሀፍ ቅዱስን ጥቅስን እንዲህ በማለት ገልጾታል “የመንግስት መስሪያ ቤቶች ቢሮዎች ጠረጴዛዎችና ኮምፒዩተሮችና ግድግዳዎች ላይ ህዝብ እንዲያገለግል የተቀመጠ ኃላፊና ሰራተኛ በራሱ እምነት ምስሎች አጨመላልቆ የምናይበት ሁኔታ…” በማለት አስቀምጦታል ፡፡ይህ ሁኔታ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ቢታይም የሰውን የእምነት ነጻነት ከማክበር አኳያ ይህን የመሰለ የማቋሸሽና የማጥላላት ጽሁፍ መንግስትን ወክሎ ወጥቶ መመልት መቻል እንደ አንድ ዜጋ ያሳፍራል፡፡ እዚህ ላይ የማህበረ ቅዱሳንን ስም በማይገባው ቦታ ከውሀቢያ እና ከአመለካከቱ ጎን አስቀምጦት ማየት ችለናል ፤ ለምሳሌ በገጽ 33 ላይ “በአንዳንድ  የኦርቶዶክስ አማኝ ነኝ ባዮች ከማህበረ ቅዱሳንም የተለየ ሚና ያለው ኮር ሃይል የሚያስተጋባው አንድ ሀገር አንድ እምነት የሚለው ቅዥት ጸረ ህገ መንግስታዊ  ነው ፡፡ ወሀብያ ይሁን የሌላ እምነት ተከታይ ጸረ ህገ መንግስት አቋሞቹንና ተግባሮችን አውግዞ እንደማኛውም ዜጋ ወይም ቡድን የራሱ መብት እንዲከበርለት የሚፈልገው ሁሉ የሌላውንም መብት አክብሮ እስካልተንቀሳቀሰ ድረስ ከህገ መንግስቱ ጋር የማይጋጭትና የእምነቱን አስተምህሮ የሆኑት ጉዳዮች ላይ መንግስት የመምረጥም የመተቸትም ፍላጎት የለውም ፤ ይህንም አድርጎት አያውቅም” በማለት ያትታል ፤ አሁን እንደ ነጥብ የማህበሩን ስምና የጽሁፉ ይዘት አብሮ የሚሄዱ ሆነው አያገኟቸውም ፤ “ሊበሏት ያሰቧትን …..” የሚባል ተረት ትዝ ያሰኞታል ፤ እኛ በርካታ የጥምቀት በዓላት ላይ ስንመለከት “አንድ ሀገር አንድ እምነት” የሚል ተጽፎ ለመመልከት አልቻልንም ፤ እነሱ ካዩ ከተመለከቱና መረጃው ካላቸው ቢያሳዩን መልካም ነው ፤ መጽሀፉ ደግሞ  አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤” ነው የሚለው “አንዲት ሀገር” የሚል የለበትም ፤ ይህ ጥቅስ ህገ መንግስቱን የሚጋፋ ቢመስላቸውም እኛ ምን ማድረግ እንችላለን ? ከህገመንግስታችሁ ጋር እናጣጥምላችሁ ? ምን እንበለው ? ምንስ ብለን ቲሸርታችን ላይ ጽፈን እንልበሰው ? እኛ ቃሉ የመፈጸም እንጂ የማስተካከል የመለወጥ መብቱ የለንም ፤ ቃሉ ደግሞ እንደማይለወጥ በግልጽ መጽሀፉ ይነግረናል ፤ እኛ የተጻፈልንን ማመን ብቻ ነው ፤ ደግመን እንበለው አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት” ስለ ሀገሩ ተውትና “አንድ ሃይማኖት” የተባለችው ቀጥተኛዋ በደም የቆየችልን አሁን እኛ ያለንባት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ናት ብለን እናምናለን ፡፡  

በሌላ በኩል በገጽ 37 ላይ ይህን ሰፍሮ ያገኙታል “በክርስትና ውስጥም በአንድ ወይም በሌላ መልኩ በተለይ ከማህበረ ቅዱሳንም የተወሰኑ ከመሰረታዊ የእምነቱ አስተምህሮ ፈንጠር ያሉ እና በመሰረቱ ጸረ-ህገመንግስት መገለጫ ያላቸው አቋሞች የተላበሱበትና አንዳንድ የእኛ አባላትና አመራሮችም ኢህአዴግነትንም ጸረ ኢህአዴጋዊ አቋሞችን የያዙ ይዘቶችንም የሚያንቀሳቅሱበት ሁኔታ በገሀድ የሚታይ ነው፡፡ አባላችን ወደ ሃይማኖት ሲሄድ ኢህአዴግነቱን ትቶ ፤ ወደ ኢህአዴግ ሲመጣ ደግሞ ሀይማኖቱን ትቶ ሊሆን አይችልም ፡፡ ጠንካራ አማኝም ጠንካራ ኢህአዴግም በመሆን መካከል ግጭት የለም ፡፡ ግጭት የሚፈጠረው ድንበሮችን ስናደበላልቅ ነው ፡፡ ስለዚህም በዚሁ አግባብ ግልጽነት ተፈጥሮ አባላችንን አመራራችን ሰልፉን ያስተካክል ፤ ለማስተካከል የሚቸገር ደግሞ በሰበባ ሰበብ ሳይሸፋፈን ከድርጅቱ መጽዳት አለበት በማለት ያስቀምጣል” ይህን ያህል አትኩሮት ሰጥቶት ማስቀመጥ ከቻለ መንግስት ጊዜው ራስ ምታት እንደሆነበት ያሳያል ፤ በብሎጋችን ላይ ከወራት በፊት የሙስሊሞችን እንቅስቃሴ በተመለከተ በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ አንዱ ፍርድ ቤቶች ውስጥ 13 የሚደርሱ ሙስሊም ጠበቃዎች እና ዳኛዎች በእለተ ቅዳሜ በአሳቻ ሰዓት ተሰብስበው መገኝታቸውን  ጽፈን ነበር ፤ ይህን ሁኔታ ከተመለከተ በኋላ “በሀይማኖት ላይ የለዘበ አቋም እንዳታሳዩ ፤ ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጋችሁ ብቻ ስራችሁን ስሩ” በማለት ቀጭን ትዕዛዝ ማስላለፉን ገልጸን ነበር ፤ አሁንም መናገር የፈለገውን ነገር ግልጽ ባለ መልኩ መናገር ባይችልም ኢህአዴግ አቋሙን ግን ሲያስቀምጥ ይመለከታሉ፡፡ ይህን የሚያገኙት ለአመራራቹ “ቀጣይ የትግል ግባችን ምን ይሁን” በሚለው ውስጥ ነው፡፡

በገጽ 17 ላይ አክራሪነት እና የመንግስት አመለካከት እንዲህ በሚል ሲያስቀምጥ እናያለን “..የሀይማኖት አክራሪነት የሚለው አገላለፅ የተለያዩ ሰዎች ከተለያዩ መመዘኛ በመነሳት ይተረጉሙታል ፡፡ የሃይማኖት መሪዎች አክራሪነትን ከሚመሩት ሃይማኖት መጻህፍት በመነሳት የቅዱሳን መጻህፍቱን  መሰረታዊ መርህዎች የሚጻረር እንደሆነ በዝርዝር ያስረዳሉ ፤ ከዚህ በመነሳት ያወግዙታል ፡፡ የሀይማኖቱ እምነት ምን እንደሆነ ከሀይማኖት መሪዎቹ በላይ የሚያውቅ የለምና እነዚህ መሪዎች ከሚያውቁት ነገር ተነስተው አክራነትን ቢተነትኑትና ቢያወግዙት መብታቸው ነው ፡፡ ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ ድርጅታችንና መንግስታችን ግን በሃይማኖት ሊቃውንት የተገነቡ ስላልደሉ አንድን ወይም ሌላ ሃይማኖትን ለማራመድ ሳይሆን ሁሉንም ዜጎች ለልማትና ዴሞክራሲ ዙሪያ ለማንቀሳቀስ የተደራጁ በመሆናቸው አክራሪነትን የሚመለከቱት ለልማትና ዴሞክራሲ አጀንዳ ካለው ተጽህኖ በመነሳት ብቻ ነው፡፡ ከዚህም አኳያ ሲታይ የሃይማት አክራሪነት ጸረ ልማትና ጸረ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ሆኖ ይገኛል ፡፡
የዴሞክራሲ ስርአታችን ሁሉም ዜጎች የእምነት ነጻነት እንዳለው ያስቀምጣል ዜጎች የራሳቸውን እምነት ነጻነት ማስከበር ይችሉ ዘንድ የሌላውን የእምነት ነጻነት ማክበር እንዳለባቸው ያስቀምጣሉ ፡፡ አክራሪነት የምንለው ይህ መሰረታዊ የዴሞክራሲ መርህ በሃይማኖት ሽፋን መቃወም ነው፡፡ ይህን የአክራሪነት አመለካከት ለሁሉም ሃይማኖቶች ሊታይ የሚችልና አልፎ አልፎም በተግባር የሚከሰት ነው፡፡ በዚሁ መሰረት አንዳንድ ሙስሊሞች ሌላውን ቀርቶ የተለየ አመለካከት ያላቸውን ሙስሊሞች እንኳን ሳይቀሩ ሀቀኛ ሙስሊሞች አይደሉም ብለው በመፈረጅ የእምነት ተቋሞቻቸውን ለማፍረስ ፤ የሃይማኖት አባቶችን መቃብሮች ቆፍረው ለማውደም ይከጅላቸዋል፡፡ በተግባር ሲፈጽሙት ታይተዋል ፡፡ የራሳቸውን የእምነት ነጻነት ለማስከበር የሚሞክሩት የሌላን ነጻነት በማክበር ሳይሆን የሌላውን ነጻነት በመድፈቅና በማፈን ነው፡፡ በተመሳሳይ አንዳንድ ኦርቶዶክስ ክርስትያኖች ሌላው ቀርቶ የተለየ አመለካከት ያላቸው ክርስትያኖችንም ቢሆን የሚከተሉትን እምነት ክርስትና አይደለም ብለው ከማመን አልፈው ፤ እነዚህ ተለየ አመለካከት ያላቸው ዜጎች እምነታቸውን በነጻነት እንዳያራምዱ በተለያየ ሽፋን ማፈን ይከጅላቸዋል፡፡” በማለት ያስቀምጣል ፤ ከላይ እንደመነሻ የተንደረደረበት ሀሳብ አክራሪነት ሲሆን ቀጥሎ ደግሞ አክራሪ ሙስሊሞችን ስራዎቻቸውን ያስቀምጣል ፤ በስተመጨረሻ “አንዳንድ ኦርቶዶክሶች” በማለት በእኛ ላይ አክራሪነትን ቋጭቶ ይደመድማል ፤ 

እኛ ተሀድሶያውያንን ተከታትለን ከቤተክርስትያኒቱ አስተምህሮ ውጪ የሆነውን ምንፍቅናቸውን ለህዝብ ስላሳየን አክራሪ ተብለናል ፤ በመሰረቱ ቤተመንግስትን በወታደር መጠበቅ ይቻላል እምነትን ግን እንደ እነርሱ በወታደር መጠበቅ አይቻልም ፤ አባቶቻችን ይችን እምነት ከመናፍቃን ጠብቀው ያቆዩልን ክፉ ትምህርታቸውን በማውጣት መክረው አልመለሱ ሲሉ በጉባኤ በማውገዝ መሆኑን እኛ እንጂ እነርሱ ሊያውቁልን አይችሉም ፤ ተሀድሶያውያንን የእምነት ነጻነታቸውን አልተጋፋንም ፤ የፈለጉትን እምነተ ማመን መብታቸው ነው ነገር ግን “ቤተክርስትያናችን የእነሱ አመለካከት ማራመጃ መድረክ አትሆንም”በማለታችን “አንዳንድ ኦርቶዶክሶች” ተብለን ስም ተሰጠን ፤ አሁን ብቻ አይደለም ወደፊትም እነዚህን መሰል የቤተክርስትያን የእግር ውስጥ እሳቶችን ስራቸውን ከመቃወም ፤ መግባርና ተግባራቸውን ከማጋለጥ ወደ ኋላ አንልም ፤ ጽሁፉ ጉደኛ ነው ብዙ ነገር አለበት እንቀጥል፡፡

የዲሞክራሲ ስርአታችን መንግስትንና ሃይማኖት መለያየት እንዳለባቸውና አንዱ በሌላው ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት እንደማይገባው በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ዲሞክራሲ ብሎ ነገር በፍጹም የማይታሰብ ነገር መሆኑን ያረጋግጣል ፡፡ የሃማኖት አክራሪነት የምንለው ይህንኑ መሰረታዊ የዲሞክራሲ መርህ  በሀይማኖት ሽፋን መናድ ነው ፤ ይህው አመለካከት በተለያየ መልኮች ሊገለጽ ይችላል፡፡ ሰፊ ቁጥር ባይኖራቸውም ጥቂት ኦርቶዶክስ ክርስትያኖች እንደ ድሮ ሁሉ ኦርቶዶክስ ክርስትና የመንግስት ሃይማኖት እንዲሆን ፤ ኢትዮጵያ የክርስትያነ ደሴት ናት ከሚል ቅዥት ባለፈ አንድ “ሀገር አንድ ሃይማኖት” የሚል መፈክር ደረታቸው ላይ ለጥፈው ለመሄድ እንኳን ሀፍረት የማይሰማቸው ሆነው በአደባባይ ይታያሉ፡፡ ከሌሎች የተለየ መብትና ጥቅም እንዲኖረው ይመኛሉ፡፡ ይህ አመለካከት ምንም እንኳን በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛው  የከሰመ ቢሆንም  አክራሪነት የሚገለጽበት አንዱ ገጽታ መሆኑ አልቀረም ፡፡ በሌላ በኩል አንዳንድ ሙስሊሞች የሀይማኖት ብዙሀነት ባለበት ሀገር እስልምና ነው ብለው ያመኑበት መመሪያ በመንግስትና በመንግስት ተቋች አማካኝነት እንዲፈጸሙ እስልምና መንግስት ሃይማት እንዲሆን ሲከጅሉ ይታያሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሁለቱም እዚህው ሀገር የተፈጠሩ ይመስል የኦርቶዶክስም ሆነ የእስልምና አንዳንድ ተከታዮች ዘንድ የሚስተዋለው የተዛነፈ አስተሳሰብ ሁለቱም ነባር እንደሆኑና ሌላው መጤ በመሆኑ የሁለቱን ያህል ስፍራ እንደማይገባቸው አድርጎ የማሰብ ነው፡፡ ሌሎችም ሀይማኖቶች ደረጃው ቢለያይም ተመሳሳይ አክራሪነት ዝንባሌ የተጠናወታቸው አባላት አሏቸው፡፡ እነዚህ የተዛነፉ አስተሳሰቦች በአደባባይ የሚነገሩ ጭምር ናቸው ፡፡ እዚህ ላይ መዋቅራችንም ለችግሩ የራሱን ድርሻ መውሰድ አለበት ፡፡ የሁሉም ዜጎች የጋራ ንብረት የሆኑ አደባባዮችና መንገዶች በየበአሉ ከኃይማት ጋር በቀጥታ ባልተያያዙ ጸያፍ መፈክሮች ሲጥለቀለቁ መዋቅራችን ጭምር አይቶ እንዳላየ የሚያልፍበት ሁኔታም ይታያል፡፡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ቢሮዎች ጠረጴዛዎችና ኮምፒዩተሮችና ግድግዳዎች ላይ ህዝብ እንዲያገለግል የተቀመጠ ኃላፊና ሰራተኛ በራሱ እምነት ምስሎች አጨመላልቆ የምናይበት ሁኔታ መንግስትና ሃይማኖትን ለመለየት የተቀመጠውን ድንጋጌ በቀጥታ በመጻረር በመሆኑ መወገዝ መወገድ የሚገባው ነው፡፡ በአንድም በሌላ መንገድ ይህንኑ አደገኛ መንገድ መከተል መደገፍ ነውና፡፡” በማለት ያስቀምጣል፡፡

ይህ ጽሁፍ በጣም ገራሚ ከመሆኑ የተነሳ ሰዳቢዎቹ ሲሳደቡ ጠያቄ እንደማይመጣ እርግጠኛ ሆነው ነው ፤እውን ኢትዮጵያ የክርስትያን ደሴት አይደለችምን ? በቁጥር የምናውቃቸው በቁጥር የማናውቃቸው ከ20ሺህ በላይ አብያተክርስትያኖቻችን ቋሚ ምስክሮቻችን ናቸው ፤ ይህ ለናንተ ቅዥት ነው የማይፈታላችሁ ነገር ነው ፤ እንደ “ማኔ ቴቄል ፋሬስ” ፈቺ የሚያስፈልጋችሁ ይመስለናል ፤ ኢትዮጵያ የክርስትያን ደሴት መሆኗ እኛ ዝም ብንል ምድሪቷ አፍ አውጥታ ትናገራለች ፤ትላንትና በእርዳታ ስም የመጡትን እምነቶች የተከፈቱትን አዳራሾች አትመልከቱ ፤  ይች ሀገር እንደ ሀገር እዚህ የደረሰችው በዚችው ቤተክርስትያን አስተዋጽኦ ነው ፤ የመጣችሁበትን መንገድ ብትረሱ ፤ የተነሳችሁበትን ማህበረሰብ ብትዘነጉ ፤ የበላችሁበትን ወጭት ብትሰብሩም ነፍስ ከስጋችሁ ስትለይ ፤ ነፍስም ፈጣሪዋን ሽታ ስትኮበልል በሞታችሁ ወቅት ግን ከ10 ሺህ ብር በላይ በቅድስት ስላሴ ቤተክርስትያን ቀብራችሁ እንዲያምር የምትፈልጉ ሰዎች ይህን ክዳችሁ ሰው እንዲክድ ብታደርጉ ይህ ታሪክ ስለሆነ መፋቅም መቀየርም መደለዝም አትችሉም ፤ ሌላው ደግሞ “ነባር አይደላችሁም” መባላችን አስገርሞናል ፤ ታሪክ ይናገራል ሙስሊም ወንድሞቻችን ወደዚች ሀገር የመጡት ከ5ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ መሆኑን ተጽፎ የተቀመጠ እነርሱም የማይክዱት ሀቅ ነው ፤ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በ34 ዓ.ም ክርስትናን የተቀበለ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መሆኑን በመጽሀፍ ቅዱስ ላይ ሰፍሮ እናገኝዋለን ፤ ታዲያ ማነው የነበረው ? ማንስ ነው በሂደት የመጣው ? ፤ ማንስ ነው መጤ ? እናንተም እኮ ለኢትዮጵያ ሳይሆን ለአዲስ አበባ መጤዎች ናችሁ ዘነጋችሁት እንዴ ? ፤ ስለዚህ የኦሪት መስእዋት ስታቀርብ የነበረችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አስጠጊ እንጂ ተጠጊ አለመሆኗ እወቁ ፤ በሌላ በኩል ኦርቶዶክሳውን ሆንን የመጽሀፍ ቅዱስን ጥቅስ በቲሸርቶቻችን ላይ አድርገን ስንሄድ ሀፍረት እንዴት እንደማይሰማን ጸሀፊው ሀሳቡን ያስቀምጣል ፤ “ነገሩ እንዴት ነው” አለች አይጥ የድመት ጓደኝነት ያላማራት ፤ ሌሎች በእምነታቸው ሊያፍሩ ይችሉ ይሆናል ፤ ሳያውቁ ገብተውበት መውጫው ጉድጓድ ጠቦባቸው ያሉበት እምነት ያሳፍራቸው ይሆናል ፤ እኛ ግን አንዳች የምናፍርበት የምንሳቀቅበት አንገት የምንደፋበት ነገር የለንም ፤ ለምንስ እናፍራለን ፤ በጣም ደስ ብሎን እንደምናደርገው በዚህ አጋጣሚ እወቁልን ፤ ለኛ ስብከት ነው ፤ ካስተዋላችሁ 4ኪሎ አካባቢ አንድ አይምሮው ትንሽ የሚያመው ወንድም ከፊት ለፊቱ ላይ  የእመቤታችንን ነገር ለመንገር “ትውልድ ሁሉ ብጽእት ይሉኛል” የሚል ጽሁፍ ሲለጥፍ በጀርባው ደግሞ አሁን የማላስታሰውን አንድ በጣም ደስ የሚል ጥቅስ በጀርባው ላይ ለጥፎ ሲዞር ተመልክቻለሁ ፤ አደራችሁን አሸባሪ እንዳትሉት ፤ እሱ ኑሮ ያሸበረው ይበቃዋል……. 

“…እዚህ አገር የተፈጠሩ ይመስል..”  ማለትስ ምን ማለት ነው ?፤ ዛሬ ጠያቂ ባይኖራችሁ ነገ ግን ይኖራችኋል ፤ ቀን የራሱን ነገር ይዞ ይመጣል ፤ ጊዜ በራሱ መፍትሄ የሚሆንበትም ወቅት ሩቅ ላይሆን ይችላል ፡፡ በምድር የማይሻር ስልጣን የማይነቀል መንግስት የለም፡፡
  
በተለያዩ የመንግስት ፤ የግል እና መንግስታዊ ያልሆነ ቢሮዎች የሚሰሩ ሰዎች የመስሪያቤታቸው ደንብና መመሪያ ባይፈቅድም የመጽሀፍ ቅዱስ ጥቅስና ቅዱሳን ስእላትን በግድግዳ ላይ ለጥፈው ይታያሉ  ፤ ነገር ግን ይህ ነገር አግባብ አለመሆኑን በመንገር የሚያወርዱበትን መንገድ ከማመላከት ውጪ “በምስሎች አጨመላልቆ የምናይበት ሁኔታ” በማለት ድርጅታዊ አቋምን በሚያንጸባርቅ መጽሄት ላይ ሰፍሮ መመልከት ያሳዝናል ያሳፍራልም፡፡ እንቀጥል..

ይህ ጽሁፍ ጽንፈኞችን በአንድ አንቀጽ አንዲህ ብሎ ይገልጻቸዋል “ሁል ጊዜም ጽንፈኞች ማንኛውም ሰው በሚከተለው እምነት የግል መብት የለውም ብለው ያምናሉ ፡፡ ውይይትና መግባባት ፤ ሰላማዊ ውይይትን በማውገዝ በአመጽ ተደግፈው የራሳቸውን አተያይ ይጭናሉ ፡፡ ከፍቅር ጥላቻን ፤ ከርህራሄ ጭካኔን ፤ ከመቻቻል መናቆርን ፤ ከእውቀት ድንቁርናን ፤ ከውይይት ጉልበትን ይመርጣሉ ፤ ያበረታታሉ ፡፡ ጽንፈኞች የመንግስትና የሃይማኖት መለያየትን አይቀበሉም ፤ ይልቅ እነሱ እምነት የተለየ የበላይነት እንዲኖረውና መንግስታዊ ድጋፍ ጡንቻ እንዲኖረው ይፈልጋሉ፡፡ ይህ አመለካከት በተለያዩ የእስልምና እና ክርስትና ሃይማኖቶች ውስጥ በመሸጉ የተወሰኑ ቡድኖች የሚስተዋልና በተለያየ መልክና ደረጃ የሚንጸባረቅ ነው፡፡” በማለት ይገልጻቸዋል ፤ አክራሪ ሙስሊሞች ሊኖሩ ይችላሉ ፤ ነገር ግን አክራሪ ኦርቶዶክስ ግን ሊኖር አይችልም ፤ ሁለታችንንም በአንድ ሚዛን አስቀምጦ በአንድ መነጽር እየተመለከቱ መጻፍ አግባብ አይደለም ፤ ባይሆን ባሳለፍናቸው ጥቂት አመታት በርካታ ኦርቶዶክሳውያን በጅማ እና እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች አክራሪ በሆኑ ሰዎች መከራን ተቀብለዋል በመቀበልም ላይ ይገኛሉ ፤ በተለይ በጅማ የበርካቶች ደም ሲፈስ መመልከት ችለናል ፤ ነገር ግን መንግስት ይህ ነው የሚባል ርምጃ ሲወስድ መመልከት አልቻልንም ፤ የተጎዳነው በደልና ግፍ የደረሰብን እኛው ሆነን ሳለን ከአድራሽ ሃይሎች ጋር ደምሮ ሂሳብ ማወራረት ተገቢ አይደለም ፤ የዛሬ ዓመት አካባቢ በጅማ አውራጃዎች ከ35 በላይ የሌሎች የእምነት ተቋማት አዳራሾቻቸው በእሳት ሲጋዩ ፤ ሰውም ሲፈናቀል በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ጆሯችን ሰምቷም ፤ ከጋዜጦች ላይም አይኖቻችን አንብበዋል ፤ የሚገርመው ነገር ግን ይህን አደረሱ የተባሉት ሰዎች ማንነታቸው ስናውቅ የመንግስን እርምጃ አለመጣጠሙ ነበር ፤ እነዚህ ሰዎች በመንግስት ስልጣን ላይ የሚገኙ ፤ የአካባቢው ባለሀብቶች ፤ የመስጂድ ኢማሞች ፤ የውጭ ገንዘብ ፈሰስ የሚደረግላቸው ቡድኖች እና የኢህአዴግ አባላት ሆነው መገኝታቸው አስደምሞናል ፤ እስኪ የደረሰውን የሞት ፤ የአካል ፤ የንብረት ፤ የሳይኮሎጂ ጉዳት አስቦ የተወሰደውን እርምጃ ተገቢ ነው የሚል ሰው ማነው ? ፤ እኛስ እውነትን እንናገራለን ጥሩውን እናበረታታለን የማይጠቅሙ አካሄዶችን እንነቅፋለን ፤ እነዚህን የመሰሉ የወረደ አመለካከት ያላቸውን ለራስ  ለቤተሰብ ለእምነት ፤ ለድርጅታችሁ ኢህአዴግ እና ለሀገር የማይጠቅሙትን ማጥራት ከውስጡም የማጽዳት ስራ መስራት ሲገባው ፤ እጁን ወደ ሌሎች ላይ መጠቆሙ የሚያዋጣ አካሄድ አይመስለንም ፡፡

ጽሁፉ ይቀጥላል…
“ በሀገራችን ዜጎች በሚከተሉት እምነት ምክንያት በሚገፉባቸው ተገደው የሌላውን ሃይማት ካልተከተሉ ከቀያቸው የሚፈናቀሉበት ፤በሚከተሉት እምነት ምክንያት በተወሰኑ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተቀጥረው ሀገራቸውን የማገልገል ፤ ከተቀጠሩም ከመሰላሉ ስር ፈቀቅ እዳይሉ ይደረግባቸው የነበሩት በነዚያ ህገ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ጥበቃ በነበራቸው ግፎች በነገሱባቸው የጨለማ ዘመናት እንኳን ጠንክሮ የዘለቀው የሃይማኖት መቻቻል ፤ ይህ ህዝቦች አብሮ የመኖር እና መደጋገፍ ትስስር ለመበጣጠስ በሀገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጽንፈኛ አክራሪ  ኃይሎች የተፈጸሙ ይጥፋት ድግሶች ማስተዋል ጥሩ ነው፡፡ ጥፋቶቹ ማተራመስ የጀመሩት በቅድሚያ የወጡባቸውን የሃይማኖት ተከታዮች ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው የተቃጠሉ እና  የፈረሱ መስጅዶች ፤ የታዋቂ የእስልምና  የመቃብር ስፍራዎች በሙሉ ጥፋት የተፈጸመባቸው እስልምናን እንከተላለን በሚሉ ጥቂት ጽንፈኞች ነበር፡፡ የሙስሊሙን ተቋማት ከማፈራረስ ሳይቦዝኑ ቤተክርስትያናት አውድመዋል፤  በክርስትና በኩል ሌላውን የሚያንቋሽሹ ፤ የተለያዩ የክርስትና ተከታዮችን ጨምሮ መናፍቃን ፤ ኢ-አማንያን በማለት የሚተነኮሱ ኃይሎች አሉ፡፡ ከሁሉም ሃይማኖቶች አንጻር  ያሉት እነዚህ ፅንፈኞች በርካታ ንጹሀን ዜጎችን አሳስተው በማነሳሳትና አንዱ በሌላው  ለመዝመት የተዘጋጁ በማስመሰል የፍጥጫ ድባብ እንዲነግስ የሚሰሩ ናቸው፡፡ በእርግጥ ከበርካቶች በስተጀርባ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ስፖንሰሮች ያሉአቸው የፖለቲካ አጀንዳ የተላበሱ ጽንፈኞች ናቸው ፡፡ ብዙሀኑ ግን ለእምነታቸው ዘብ የቆሙ እየመሰላቸው በቀላሉ ሊሳሳቱ ይችላሉ፡፡ …. ወሃቢያን ወይም ሌላው የመከተል የማህበረ ቅዱሳንን ወይም ሌላ አተያይ የመያዝ መብት የዜጎች ነው ፡፡ መንግስት ሊመርጥላቸው አይችልም፡፡”በማለት ይቀጥላል ፤ የበፊቱን የመንግስ አገዛዝ ማስቀመጣቸው ተገቢ ነው ፤ ቤተክርስትያችንም ከመሀመድ ግራኝና ከዮዲት ጉዲት በኋላ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ወቅት ነው ፤ በጊዜው ከአሁኑ የተሻለ የሀይማኖት መቻቻል እንደነበረ ጊዜው ያሳለፉ ሰዎች ምስክሮች ናቸው ፤ ነገር ግን ያሳለፍነው ጊዜ ምንኛ ጨለማ ቢሆንም ይህን ወቅት ብርሀን ለማለት የሚያስደፍር ሁኔታ ግን የለም ፤  ሚዛኑ የመድሀኒአለም ነውና እኛ ዝም እንላለን ፤ 


በተጨማሪ በጥቅምት 11 ላይ ተሀድሶያውያንን በመቃወም ፤ ቤተክርስትያን አትታደስም በማለት ከአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች እንደ ንብ በመትመም የተቃወሙትን ወጣቶች ሁኔታ ሌሎች የፖለቲካ አላማ ያላቸው ሰዎች ያነሳሷቸው ናቸው ብሎ ጽሁፉ ያትታል ፤ ይህ ስለ ቤተክርስትያናቸው ብለው ያደረጉት እንጂ የፖለቲካ ጥማት ያለባቸው ሰዎች ገፋፍተው ያስወጧው አይደሉም ፤ በጊዜውም ተቃውሟቸውን የገለጹት ፍጹም ኦርቶዶክሳዊ በሆነ መንገድ መዝሙር በመዘመር እና እነዚህ ሰዎች ላይ አለን የሚሉትን የቤተክርስትያኒቷ አስተምህሮ ያልሆኑትን መረጃዎች ለብጹአን አባቶቻችን በማቅረብ እንጂ ከውጭ ሀገር የገንዘብ እርዳታ ተደርጎላቸው የፖለቲካ ማራመጃ ሆነው አይደለም ፤ ተቃውሞው የተደረገው በቤተክርስትያን ግቢ እንጂ በቤተመንግስት አለመሆኑን እናተም የምታውቁት ይመስለናል ፤ በጊዜው የነበሩት የሰንበት ተማሪዎች ለእምነታቸው ዘብ ቆመዋል ፤ የአባቶቻቸው እምነት እንዳይሸረሸር ድምጻቸውን ማሰማት ችለዋ ፤ ፍጹም አልተሳሳቱም ፤ ለእምነት መቆርቆርን ያሳዩን ያስተማሩን አይከኖቻችን ናቸው ፤ በሌላ በኩል “መናፍቃን” የሚለውን ስም ባለቤቶቹ ሳይከብዳቸው መንግስት የገደል ማሚቱ ሆኖ ያስተጋባላቸዋል ፤  እናንተ አባል ያልሆነን አሸባሪ በማለት ታፔላ ስትለጥፉ ምንም ያልመሰላችሁ እኛ ግን ውስጣችንን እንደ ነቀዝ ቦርቡረው ሊጨርሱን ጥቂት የቀራቸውን ሰዎች የሚመለከተው አካል ስራቸውን መዝኖ ሲያወግዛቸው እኛም መናፍቃ ነበሩ ስንል ለምን ትሉናላችሁ ፤ ህገ መንግስቱን ይጋፋል ትላላችሁ ፤ ይህ ህገ መንግስት እኮ ለሁሉም ነው የሚሰራው ፤ መፎከሪያ ማስፈራሪያም ሆኖ መቀመጥ የለበትም፤ ለማንኛውም በመጽሀፉ ላይ ከሰፈሩት 41 ገጾች ውስጥ 30 ያህሉ ሙስሊሞችን የሚመለከት ሲሆን 10 ደግሞ ቀስቱ ወደኛ ሆኖ አግኝተነዋል ፤ ዋና ሀሳብ ያልናቸውን በጣም በጥቂቱ ለማሳየት ሞክረናል ፤ መጽሀፉን የምታገኙ ሰዎች አንብቡትና የራሳችሁን ፍርድ ስጡ ፤ በቅርብ ለማታገኙት በሀገር እና ከሀገር ውጪ ላላችሁት ደግሞ መለስ ብለው ብሎጋችንን ይጎብኙ እንደወረደ በፒዲፌ አዘጋጅተን ብሎጋችን ላይ እናስቀምጥሎታለን …….

አንብባችሁ ሀሳባችሁን ላኩልን…..

አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤”  ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4፤5

No comments:

Post a Comment