Thursday, August 16, 2012

(ሰበር ዜና) ቅዱስ ፓትርያርኩ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ


ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ዛሬ ሌሊት ዐረፉ

from Daniel kibret's views'

                            ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ዐርፈዋል፡፡ 
እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ይማር
ብጹዐን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናትና ምእመናን ይህ ነገር በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ያልታሰበ አደጋ እንዳያመጣ ጥንቃቄ የተሞላ ሃይማኖታዊና ጥበባዊ ሥራ መሥራት አለባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ አራት ነገሮች እንዳይፈጠሩ ጥንቃቄ ያስፈልጋል
  1. የእርሳቸው ደጋፊና ተቃዋሚ በሆኑ አካላት መካከል በሚፈጠር ግጭት ቤተ ክርስቲያኒቱ እንዳትታወክ
  2. ሀብት እና ቅርስን የማሸሽ አዝማሚያ እንዳይከሰት
  3. ቤተ ክርስቲያኒቱን ማን ለጊዜው ይምራት በሚለው ዙርያ በሚፈጠረው ልዩነት አደጋ እንዳይከሰት
  4. በቀጣይስ ማን በወንበሩ መቀመጥ አለበት በሚለው ዙርያ ችግር እንዳይከሰት
አሁን የመረጋጊያ ጊዜ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ምንም ዓይነት ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ለፓትርያርኩ የኀዘን ጊዜ ያውጅ፡፡ ጊዜያዊ ኮሚቴ ያቋቁም፡፡ ነገሮችን በግልጽነት ለሕዝቡ ይፋ ያድርግ፡፡ ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ልምድ ይውሰድ፡፡ ማንኛውም የፓትርያርኩ ንብረቶች ወደ ሌሎች ከመጓዛቸው በፊት በጥብቅ ይቀመጡ፡፡ የባንክ ሂሳቦች ይዘጉ፡፡
አሁን የመረጋጊያ ጊዜ ነው፡፡ ለሀገሪቱም ሆነ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሲባል ቤተ ክርስቲያኒቱን በዚህ ሁኔታ ወደ ጸጥታ ወደብ የሚመራ አመራር ያስፈልጋል፡፡
ዝርዝሩን እንመለስበታለን፡፡


አቡነ ጳውሎስ ………

(አንድ አድርገን ነሐሴ 10 2004ዓ.ም)፡- አቡነ ጳውሎስ በጠና መታመማቸውን ትላንትና ገልጸን ነበር ፤ ዛሬ ደጀ-ሰላም እንደገለጸችው ‹‹Unconfirmed Deje Selam sources say Patriarch of the Ethiopian Orthodox Tehwadeo Church, His Holiness Abune Paulos, is dead. Stay Tuned for the detail.›› በማለት ተዘግቧል ፤ መረጃው ትክክለኝነቱን ለማረጋገጥ የቤተክህነቱን ድምጽ መስማት መልካም ይመስለናል ፤  ለማንኛውም ለሙሉ ዘገባ የቤተክህነቱን ድምጽ ኦፊሺያል በሆነ መልኩ  ሲገለጽ እኛም እሱን እናቀርባለን፡፡
(ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 10/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 16/ 2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ ኻያኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸውን ከሐምሌ 5 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ወሩ መገባዳጃ ሲያከበሩ የቆዩት አምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በጠና ታመው ነሐሴ 8 ማምሻውን ወደደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ከገቡ በኋላ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ማረፋቸውን ምንጮቻችን እየገለጹ ነው። አቡነ ጳውሎስ በምንገኝበት የፍልሰታ ለማርያም ጾም የሰሞኑ ውሏቸው በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ጸሎተ ቅዳሴ ላይ እንደነበሩ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን ፓትርያርኩን ለሕልፈት ያበቃውን ሕመም ለይተው አልገለጹም፡፡

እግራቸው ከጉልበታቸው በታች በከፍተኛ ደረጃ መጎዳቱንና የጤናቸው ኹኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ የሚነገርላቸው ፓትርያርኩ÷ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደሚስተዋለው የአባ ጳውሎስ መውጣትና መግባት ግራና ቀኝ በሚይዟቸው ሰዎች ድጋፍ እንደሚከናወን የተዘገበ ሲሆን ራሳቸውን ችለው መራመድ ይኹን ከመኪናቸው መውጣትና መውረድም እንደተሳናቸው ተመልክቷል፡፡ አቡነ ጳውሎስ ለረጅም ጊዜ ሕመማቸውን ሲከታተሉ በቆዩበት የደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ዶክተሮች ከፍተኛ ክትትል ላይ መኾናቸውንና አስጊ በሚባል ኹኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ምንጮችን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ደጀ ሰላም ዜናውን እየተከታተለች ማቅረቧን ትቀጥላለች።

ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment