Monday, June 25, 2012

የእመቤታችን ተዓምር


(አንድ አድርገን ሰኔ 18 2004 ዓ.ም)፡- ቀኑ እለተ ሰንበት ሰኔ 17 2004 ዓ.ም  ፤ ሰንበት እንደመሆኑ የት ሄጄ እንደማስቀድስ ሳወጣ ሳወርድ ውስጤ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያር ገዳም ቤተክርስትያን እንድሄድ አመላከተኝ ፤ ቦታው ጦር ኃይሎች ወደ ወይራ-ቤተል ሲሄዱ አጉስታ ልብስ ስፌት ፋብሪካ አለፍ ብሎ የምትገኝ ቤተክርስትያን ናት ፤ በጣም በጠዋት በመነሳት ካህናት ቅዳሴ ሳይገቡ ለመድረስ ተጣደፍኩኝ ፤ እንደ ሃሳቤም ተሳቶልኝ ቅዳሴ ሳይገቡ መድስረስ ቻልኩኝ ፤ ቅዳሴው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ደስ በሚያሰኝ እኛ ውስጥን ሀሴት በሚሞላ መልኩ ቅዳሴው ተጠናቀቀ ፡፡ ከዚያ ቅዳሴው ከተጠናቀቀ በኋላ የቀኑ ተዓምረ ማርያም ተነበበ ፤ ምዕመኑ ሁሉ ቆሞ ፍጹም በሆነ ፀጥታ የእመቤታችንን ተዓምር አደመጠ፡፡


የእለቱን ትምህርት የቤተክርስትያኒቱ አስተዳዳሪ ካስተማሩ በኋላ መርሀ ግብር መሪው “ትንሽ ቆዩ ምዕመናን አንድ የምትሰሙት ተዓምር ስላለ  ስርዓቱ ሳይጠናቀቅ ወደ ቤታችሁ አትሂዱ” በማለት ሲናገር  ፤ ምን ይሆን? በማለት ትንሽ ለመቆየት ሞከርኩኝ ፤ በስተመጨረሻ የዕለቱ ወንጌል ለምዕመኑ ተሰብኮ ከተጠናቀቀ በኋላ የእለቱን ተዓምር እንዲህ በማለት መናገር ጀመረ “አንድ እናታችን ልጃቸው አይኗን ማየት ከተሳናትና ከጋረዳት ቀናት ተቆጥሮ  ነበር ፤ እናታችንም ለእመቤታችን እባክሽ እመቤቴ ይችን ልጅ አይኗን ግለጭላት ፤ አዛኝተ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ እባክሽን ከሚያዩት ተርታ አሰልፊያት ፤ እመቤቴ እባክሽን ውለታሽን መክፈል ቢያቅተኝም በእምነቴ እንድጸና እና አንዳልናወጽ የዚችን ብላቴና አይኗን አብሪልኝ” ፤ በማለት ከእንባ ጋር በቤተክርስትያኒቱ ተገኝተው ለመኗት ፤ “አንገት የማታስደፋ ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎታቸውን ባደረሱ በቀናት ጊዜ ውስጥ ልጅቷ አይኗ ማየት ቻለ”  በማለት የተደረገውን ተዓምር ተናገር  ፡፡ ከዚያ በመቀጠል “ለክብሯ መግለጫ 200 ብር እና አንድ ፓኮ ሻማ አስገብቻለሁ ብለዋል  ወንዶች በጭብጨባ ሴቶች በእልልታ አመስግኑ” ሲል ግቢው በእልልታ እና በጭብጨባ ደመቀ፡፡ እንዴት ደስ ያሰኛል “ላመነ ሁሉ ይደረግለታል” ማለት ይህ መሆኑን በእለቱ ተረዳሁኝ በእለቱ አንድ የእመቤታችንን ተዓምር “ከተዓምረ ማርያም” ላይ ስሰማ ሁለተኛ ደግሞ እኔው ባለሁበት ወቅት የተደረገ የእመቤታችንን ገቢረ ተዓምርን በመስማቴ እየተደመምኩኝ ወደ ቤቴ አመራሁኝ ፡፡ እኔ የሰማሁትን ብጽፈውና ብዙ ሰዎች ቢያውቁት መልካም ነው በማለት እንዲህ ጻፍኩላችሁ… በዚህ ወቅት ይችህ ቅኔ ትዝ አለችኝ
ውዳሴ ማርያም ሲታደል
ብርሃንን ለኔ በል
የዚህ ቅኔ ሰሙ “ውዳሴ ማርያም ሲታደል ‹‹ብርሃን›› የሚባለውን ክፍል ለኔ ስጠኝ ፤ እሱ እንዲደርሰኝ አድርግ” ማለት ሲሆን ወርቁ ደግሞ “ዓይኔን አብራልኝ ብርሃንን ስጠኝ” እንደ ማለት ነው፡፡ ወንጌል ላይ ደግሞ  እንዲህ የሚል ታሪክ እናገኛለን

“ሲያልፍም ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር የሆነውን ሰው አየ።ደቀ መዛሙርቱም። መምህር ሆይ፥ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ወይስ ወላጆቹ? ብለው ጠየቁት።ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰ። የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም። ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች። በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ። ይህን ብሎ ወደ መሬት እንትፍ አለ በምራቁም ጭቃ አድርጎ በጭቃው የዕውሩን ዓይኖች ቀባና።ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ አለው፤ ትርጓሜው የተላከ ነው። ስለዚህ ሄዶ ታጠበ እያየም መጣ።” የዮሐንስ ወንጌል 9 1-9
አሁንም ተመሳሳይ  ከ20 መቶ ዓመታት በፊት የተከናወነ በዘመናችን እየተፈጸመ ይገኛል ፤ ከዚህ ቀደም ጻድቃኔ ማርያም ለ6 ወራት ያህል የተለያዩ የህክምና ተቋማት ስትመላለስ የነበረች አንዲት የ12 ዓመት ልጅ የእመቤታችን እምነቷን ከጸበል ጋር በመደባለቅ በዓይኗ አካባቢ በመቀባት ቦታውን በረገጠች በሶስተኛ ቀኗ ማየት የተሳነው አይኗ ማየት መቻሉን ቦታው ላይ በመገኝት መመልከት ችያለሁ ፡፡ መዝሙረ ዳዊት 66 ፤20 ላይ  “ምሕረቱንም ከእኔ ያላራቀ እግዚአብሔር ይመስገን” ይላል፡፡  

“ ምህረቱን ከእኛ ያላራቀ እግዚአብሔር ይመስገን…….”
ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያር ገዳም ቤተክርስትያን ግቢዋ ብዙም ሰፊ የሚባል አይደለም ፤ በአሁኑ ሰዓት አስር ሜትር በአስር ሜትር ስፋት ባለው በቆርቆሮ በተሰራ ቤተክርስትያን ውስጥ ነው ታቦተ ህጉ ያለው ፤ አሁን ግን እየተሰራ ያለው ቤተክርስትያን 10 ሚሊየን ብር ይጥቀመው አይጥቀመው ባለሙያዎች ብቻ ነው ማወቅ የሚችሉት ፤ በጣም ትልቅ ቤተክርስትያን በአሁኑ ሰዓት እየተሰራ ይገኛል ፤ በ2001 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ መሰረተ ድንጋዩ በአቡነ ጳውሎስ አማካኝነት እንደተጣለ የተቀመጠው ድንጋይ ላይ ያረፈው ጽሁፍ ይናገራል ፤ በመሰራት ላይ ያለው ቤተክርስትያን ከ50 በመቶ በላይ መጠናቀቅ ችሏል ፤ ግቢው ውስጥ ጸበል በመኖሩ ዘወትር ጠዋት ጸበልተኞች ለመጠመቅም ሆነ ለመጠጣት ሲሰለፉ ማየት የዘወትር ተግባር ነው ፤ በሽተኞች ከድዌያቸው እየተፈወሱ ይገኛሉ ፤ መንፈስ ያደረባቸው ወንድም እህቶቻችንም የያዛቸው መንፈስ በየጊዜው በጸበሏ አማካኝነት ነጻ እየወጡ ይገኛሉ፡፡  

ይህን ላሰማህኝ ይህን ላሳየህኝ አምላክ ተመስገን……

No comments:

Post a Comment