በአንድ አይናችን በቤተክርስትያን በአንዲት እምነታችን በተዋህዶ አትምጡብን
(አንድ አድርገን ግንቦት 30 ፤ 2004ዓ.ም)፡- በቤተል ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን በቦታ ጉዳይ በተነሳው ግጭት በርካቶች ተጎድተዋል ፤ በዚህ ቦታ ይገባኛል በማለት ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማው ህጋዊ ካርታ ሲኖረው ቤተክርስትያኒቱም ህጋዊ ካርታ እጇ ላይ ይገኛል ፤ የአካባቢው ሰው በቦታው አማካኝነት ክፉኛ ስለተበሳጨ የሚሆነውን ነገር ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በአትኩሮት ሲከታተል ነበር ፤ ማክሰኞ እለት በልበ ሙሉነት ምንም እንደማይሆኑ ከክፍለከተማ የተወከሉ ሰዎች እና ጥቂት ፖሊሶች ስራቸውን ቦታው ላይ ሲጀምሩ ተቃውሞ ከምዕመኑ ማስተናገድ ጀመሩ ፤ የነበረውን ሰው ለመበተን ሲሞክሩ በያዙት የፖሊስ ሀይል ስላቻሉ ተጨማሪ የፖሊስ ኋይል ከአካባቢው ጣቢያ እንዲመደብላቸው በመጠየቅ ከ40 የሚበልጡ ፖሊሶች በአካባቢው ላይ ከደቂቃዎች በኋላ መምጣት ችለው ነበር ፤ እነዚህ ፖሊሶች የመጡት ከአንድ መሳሪያ እና ከፖሊስ ዱላ ጋር ብቻ ስለነበረ ከህዝቡ የሚወረወረውን ድንጋይ መቋቋም ሲያቅታቸው ለፌደራል ፖሊስ አድማ በታኝ ልዩ ኋይል በመገናኛ ሬዲዮ በመነጋገር የችግሩን ጥልቀት በማስረዳት ኋይል እንዲጨመርላቸው ጥያቄ አቀረቡ ፤ በዚህ ጊዜ በቦታው ላይ የነበረው ፖሊስ ወደ አርባ ቢጠጋም የህዝቡን ተቃውሞ ግን መመከት አልቻሉም ነበር ፤ ይህ የሚያሳየው ከ40 በላይ ፖሊሶች መቆጣጠር ያልቻሉት የህዝብ ተቃውሞ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ነው፡፡
የፌደራል አድማ በታኝ ፖሊስ የኃይል ጭማሪ ጥያቄ ቢቀበልም ቦታው ላይ ለመድረስ ግን ብዙ ደቂቃዎች ወስደዶበት ነበር ፤ ምክንያቱም የተነገራቸው ቦታ በመሳት ኮልፌ ቀራንዮ ወደ ወይብላ ማርያም ቤተክርስትያን አካባቢ በማምራት ችግሩ የተፈጠረበትን አቅጣጫ ባለማወቅ ቶሎ መምጣት አልቻለም ነበር ፤ ይህ አድማ በታኝ በቶሎ ቦታው ላይ ቢደርስ ኖሮ በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደርስ እንደነበር ይታመናል ፤ አድማ በታኝ ቦታው ላይ እስኪደርስ ድረስ ህዝቡ ፖሊሶቹ ላይ ባደረሰው ከፍተኛ ጉዳት 8 ፖሊሶች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው በአሁኑ ወቅትም በሆስፒታል የሚገኙ ሲሆን ቀሪዎቹ ከ25 የሚበልጡ ፖሊሶች ቀላልና መካከለኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው የደረሰን መረጃ ያመላክታል ፤ ይህ ኃይል ቅዳሴ ሳያልቅ ቤተክርስትያኑ አካባቢ ሲደርስ ብዙ ጉዳት ደርሶ ነበር ፤ አድማ በታኝ ፖሊስ ሰዎችንም ለመያዝ ቤተመቅደስ ድረስ እንደገባም ለማወቅ ችለናል ፤ ይህ ነገር ከዚህም የባሰ ሁኔታ እንዳይፈጠር በጊዜው ከባድ የሚባል በረዶ የቀላቀለ ዝናብ በመዝነቡ ሁኔታውን ከማረጋጋት አኳያ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል ተብሏል፤
ህይወቱ ያለፈው ፖሊስ በአሁኑ ሰዓት ብር እየተሰበሰበለት(ለትራንስፖርት) ወደ ትውልድ ሀገሩ ሻሸመኔ ሬሳውን ለመላክ ስራ እየተሰራ መሆኑን ለማወቅ ችለናል፡፡ በጊዜው በጣም በርካታ ሰዎች ቤት ለቤት እየታደኑ ታስረዋል ፤ይህን የምዕመኑን ተቃውሞ ፖሊስ በጊዜው በተነሳ ፎቶዎችንና ቪዲዮዎችን እየተመለከተ ትላንት ረቡዕ ሲቪል የለበሱ የፖሊስ አባላት ቤት ለቤት በመዞር የሚፈልጓቸውን ሰዎች እየያዙ ይገኛሉ ፤ በጠቅላላ በሁለቱ ቀናት ከ100 በላይ ሰዎች በእስር ላይ ይገኛሉ ፤ ሞተ የተባለው ፖሊስ በራሳቸው በፖሊስ አባላት ወደ ህዝቡ በተተኮሰ ጥይት ነው የሞተው የሚሉ ሰዎች ሲኖሩ ፖሊስ ደግሞ መሳሪያ የያዘ ሰው ነበር በማለት ገደለ የተባለውን ሰው ለማግኝት እየፈለገ መሆኑን ለማወቅ ችለናል ፤
ይህ ሁኔታ በመፈጠሩ ያላዘነ ሰው በአካባቢው የለም ፤ምዕመኑ ከመንግስት ጋር እልህ ውስጥ መጋባት አይፈልግም ፤ “አይድረስብን” ብቻ ነው መሰረታዊ ጥያቄው ፤ “የመጣውን ሁላ እንደ አመጣጡ እንችለዋለን በአንድ አይናችን በቤተክርስትያን በአንዲት እምነታችን በተዋህዶ ግን አትምጡብን”ነው የሚለው ፤ መንግስትም አልሸነፍ ባይነት ክፉ ጸባይ ስለተጠናወተው ከተፈጠረው ነገር መማር የፈለገ አይመስልም ፤ አሁንም በገደለው ሳይሆን በሞተበት አባል ክፉኛ ተበሳጭቷ ፤ አሁንም እኛ የምንለው ነገር ቦታው የቤተክርስትያኑ እንደሆነ የካርታ ማስረጃ አለ ፤ ስለዚህ መንግስት ይህን ወስዶ ለራሱም ሆነ ሌላ ሶስተኛ አካል ማስተላለፍ የለበትም ፤ ቦታውን ይመልስ ፤ ይህ ቤተክርስትያን በአካባቢው ቤቶች ከመሰራታቸው በፊት ቤተል የሚባል ሰፈር ከመቆርቆሩ በፊት አሁን የያዘውን ሁለት እጥፍ የሚያህል ቦታ ነበረው ፤ ጊዮርጊስን ከ15 ዓመት በፊት የምታውቁት ሰዎች ለዚህ ምስክሮች ናችሁ ፤ በጊዜው በቦታው ላይ ቤቶች ሲሰሩ የተወሰደው ቦታ ይበቃል ፤ በ1985 አሊ አብዶ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከንቲባ እያለ በአየር ጤና ኪዳነምህረት ቤተክርስትያን ላይ የደረሰውን ነገር እያስታወሳችሁን ቁስላችንን አትነካኩት ፤የቤተክርስትያኒቱን የመቃብር ቦታ እየወሰዳችሁ መቃብራችሁን አታርቁት ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የጸበል ፤ የታቦት ማደርያ ፤ የቀብርና መሰል ስፍራዎቿን ባላት ህጋዊ የካርታ ፍቃድን መሰረት በማድረግ በግንብና በቆርቆሮ ማጠር ቢያቅታት እንኳን በሽቦ ክልሏን ትጠር ፤ ይህን የመሰለ ችግር ወደፊት ማስተናገድ የማንፈልግ ከሆነ ይህ የመፍትሄ አቅጣጫ ነው ብለን እናምናለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ “በባቦጋያ መድሀኒዓለም በአቶ ጌታቸው ዶኒ አማካኝነት ለአቶ ታዲዮስ የኩሪፍቱ ሪዞርት ባለቤት የተሰጠው ቦታ መሰል ብጥብጥ በቦታው ላይ ከመከሰቱ በፊት ቤተክህነቷም ሆነ መንግስት የአካባቢውን ህዝብ ጥያቄ በማድመጥ ተገቢውን መልስ ይስጡ ፤ የታፈነ ጥያቄ ፤ በምዕመኑ ውስጥ መብላላትን ይፈጥራል ፤ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን ለማስመለስ ምዕመናን ይህን መንገድ እንዳይከተሉ ቀድሞ መሰራት ያለባቸውን ስራዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር ይሰራ ፤ ጥያቄዎች መፍትሄም ያግኙ ፤ ቤተክህነት ጉዳዩን ጉዳዬ ብላ ባትይዘው ፤ መንግስትም የምዕመኑን ጥያቄ እየረገጠ ካለፈ ህዝቡ ይህን መንገድ መከተል ግድ ይለዋል ፤ ቤተክህነት ፤ የክፍለ ከተማ አስተዳደር ሃላፊዎች ፤ አዲስ አበባ መስተዳድርና መንግስት ሁላችሁም የቆማችሁበትን ቦታ አስተውሉ ….‹‹ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ›› 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች…. ” መልዕክታችን ነው፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ እና በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ንፋስ ከዚህ በፊት ተከስቶ ባልታየ መልኩ ሲነፍስ መመልከት ችለናል ፤ የሚነፍሰው ንፋስ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ሰዎች መቋቋም ሲያቅታቸውና ሲወድቁም ተመልክተናል ፤ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ኢትዮጵያ ሬዲዮ ፤ ሬዲዮ ፋና እና መሰል ጣቢያዎች የሜትሪዎሎጂ ሰዎችን በማነጋገር ሳይንሳዊ መልስ ለመስጠት ሞክረዋል ፤ ‹‹ንፋስ ሲነፍስ›› አናት አባቶቻችን ለሀገር ጥሩ አይደለም በማለት ይናገራሉ ፤ አሁንም እያየን እና እየሰማን ያለነው ነገር ለማንም የማይበጅ ነገር ነው ፤ ዋልድባ ላይ ከባድ ችግር አለ፤ አሁን በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያ የተፈጠረ ችግር አለ ፤ በተጨማሪ ባድመ አካባቢ ሁለቱ ዝሆኖች ነገር እየተፈላለጉ መሆኑን አንድ ትምህርት ቤት ጉዳት እንደደረሰበትና ከሪፖርተር ጋዜጣ ላይ አነበብን ፤ ቪኦኤ ላይም የሆነውን እና የተደረገውን አደመጥን …… እረ ጎበዝ እንዴት ነው ነገሩ…
እግዚአብሔር ቤተክርስትያናችንንና ሐገራችን ከክፉ ነገር ይጠብቅልን ……
ሌሎች መረጃዎች አሉ ፤ ጊዜው ሲፈቅድ እናወጣዋለን
No comments:
Post a Comment