‹‹ትልቁ ሀብታችን ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ነው›› አቡነ ጳውሎስ
*Reporter* ትናንት በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ በ‹‹ግብረሰዶምና ተያያዥ ማኅበራዊ ቀውሶች›› ላይ ለመነጋገር በተጠራው አገራዊ ኮንፈረንስ የተገኙት የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የፓርላማ አባላት፣ ወጣቶችና ሌሎች የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ‹‹ግብረሰዶምንና ግብረሰዶም የሚያስፋፉ ምዕራባዊያንን›› አወገዙ፡፡ በዚሁ ታሪካዊና አንገብጋቢ በተሰኘው አገራዊ ኮንፈረንስ ላይ ከ2,000 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ አምስቱ ዋና ዋና የሃይማኖት ተቋማት የኦርቶዶክት ተዋህዶ፣ የእስልምና፣ የካቶሊክ፣ የወንጌላዊት መካነ ኢየሱስና የወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ያወጡትን የግብረሰዶማዊነት የተቃውሞ መግለጫ በአንድ ድምፅ እንደግፋለን ብለዋል፡፡ ግብረሰዶማዊነትን ካልተቀበላችሁ በማለት የሰብዓዊ መብት ጥያቄ የሚያነሱና ዕርዳታ እንከለክላለን ለሚሉ የምዕራብ አገሮችም ‹‹ዕርዳታቸው በአፍንጫችን ይውጣ›› የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በስብሰባው ላይ የተገኙት የሃይማኖት ተቋማትን በሙሉ ወክለው ጉባዔውን በፀሎት የከፈቱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስ፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት ሕግ ሳይጻፍ ጊዜ ጀምሮ ከእግዚአብሔር ጋር ትውውቅ ነበራቸው፤ የዛሬ ሳይንቲስቶችም ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ መሆንዋን ይናገራሉ፤›› በማለት በዓለም ላይ ያሉ ሕዝቦች በሙሉ እርስ በርስ ተረጋግጠዋል፤ ብቸኛ ነፃ አገር ኢትዮጵያ ነች ብለዋል፡፡ ‹‹አሁንም የተረገጡትና የማንነት ቀውስ ያለባቸው ወገኖች ተናገሩ ብላ የምትሰማ አይደለችም፡፡ ባህላችን አልተለወጠም፣ ታሪካችን አልተቀነሰም፣ ማንነታችን አልተበረዘም፤ እንዲሁ ዝም ብለን የምንለወጥ አይደለንም፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
ንግግራቸው በከፍተኛ ጭብጨባ የታጀበው አቡነ ጳውሎስ፣ በተለይ የግብረሰዶማውያንን መብት ካላከበራችሁ ዕርዳታ እንከለክላለን ለሚሉት፣ ‹‹ማንም ይሁን ማንም ታላቅነቱና ሀብታምነቱ ለራሱ ነው፡፡ እኛን ዝም ብሎ ድሆች አድርጎ አልፈጠረንም፤ ትልቁ ሀብታችን ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ነው፡፡ ሕዝባችን በእግዚአብሔር እምነት የሚኖር ነው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የስብሰባው አዘጋጅ ድርጅት ‹‹ዩናይትድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ›› ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሥዩም አንቶንዮስ ባቀረቡት ጥናት መሠረት፣ የግብረሰዶም ድርጊት ምንጭ የአስተዳደግ ችግርና ማኅበራዊ ቀውስ ነው፡፡ ሆኖም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮንና ሌሎች ምዕራባዊያን፣ የአፍሪካ መሪዎች የግብረሰዶማውያን መብት በአፍሪካ እንዲከበር አለበለዚያ ዕርዳታቸውን በመቋረጥ ተፅዕኖ እየፈጠሩ መሆናቸውን የመሪዎቹን የተለያዩ ጊዜያት ቀጥታ ንግግር በማሰማት በማስረጃነት አቅርበዋል፡፡
የተመድ ዋና ጸሐፊ ባንኪ ሙን ጭምር ስብሰባው በተደረገበት በዚያው የስብሰባ አዳራሽ የአፍሪካ መሪዎች የግብረሰዶማያውያን ሰብዓዊ መብት እንዲያከብሩ መጠየቃቸውን አስታውሰው፣ ምዕራባዊያን የራሳቸው የማንነት ቀውስ የፈጠረውን ቆሻሻ ባህል በአፍሪካ ለማስፋፋት ከዕርዳታ ጋር ማያያዛቸው አሳፋሪ ተግባር ነው ብለውታል፡፡ በጉዳዩ ላይ ምርምር አደረግን ያሉ የጠቃቀሱዋቸው አንዳንድ ምሁራን ባዮችም፣ ከሞላ ጎደል ራሳቸው ግብረሰዶማውያን ሆነው ከመገኘታቸውም ባሻገር፣ ከሃይማኖትም ሆነ ከተፈጥሮ ሕግ አንድም ተጨባጭ መረጃ አለማቅረባቸውን አውስተዋል፡፡
የአስተዳደግ ችግር፣ የፆታ ማንነት ቀውስ፣ ወሲባዊ ጥቃትና ሌሎችን እንደ መንስዔ የጠቃቀሱት ዶ/ር ሥዩም፣ ግብረሰዶማውያን ይጠቀሙባቸዋል ያሉዋቸውን አንዳንድ አስነዋሪ ድርጊቶችን አሳይተዋል፡፡ በቀዶ ሕክምና ዕርዳታ በፊንጢጣቸው ገብተው አንጀታቸው ውስጥ ቆይተው የተገኙ አደገኛ ነገሮችን አሳይተዋል፡፡ ‹‹ግልጽ የውጭ የባህል ወረራ ነው ያሉት›› ዶ/ር ሥዩም፣ ግብረሰዶማዊነት ኤችአይቪ/ኤድስን ጨምሮ ለተለያዩ በሽታዎችና የሥነ ልቦና ቀውስ እንደሚዳርግ አብራርተዋል፡፡
በማጠቃለያቸውም፣ ‹‹አንዴ በዚህ ችግር የተጠቁ ኢትዮጵያዊያንን በምክር መርዳት አለብን፤›› ያሉ ሲሆን፣ ከዚህ በተረፈ ግን፣ ‹‹ኢትዮጵያ የግብረሰዶም መቃብር እንጂ መፈልፈያ አትሆንም›› ብለዋል፡፡ ‹‹ችግሩ የዓለም ሕዝብ አደጋ ነው፤ ኢትዮጵያ ግን ፈውስ አለ ብለው የሚመጡባት አገር ትሆናለች፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡
‹‹ሰው ከሕግ በታች የሚኖረው በሕይወት ካለ ብቻ ነው›› ያሉት አቡነ ጳውሎስ፣ ‹‹የተፈጥሮ ሕጋችንና የተከበረ ባህላችን ይጠበቅልን ነው የምንለው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የተከበረውን የሰው ልጅ ክብር የሚነካ ስለሆነ በአስቸኳይ እንዲገታ እንፈልጋለን፡፡ የተሳሳቱ ካሉም እኔና እኔን መሰል በአስተማሪነት ላይ የምንገኘው ነው የምንወቀሰው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር በዓለም ላይ ያሉትን እንጨቶችም ሴትና ወንድ አድርጎ ነው የፈጠራቸው፡፡ አለበለዚያ እንዴት እንራባለን?›› በማለት በሰው ልጅ ላይ የመጣ አደጋ መሆኑን አሳስበዋል፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች ማኅበርን ወክለው የተገኙት አባት አርበኛ በበኩላቸው፣ ‹‹ወደ ምድር እንድንመጣ የፈቀደው እግዚአብሔር እኛ ሳንጠይቀው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጥሮናል፡፡ ይኼን ቅዱስ ቃል ሊሽሩ የመጡ ሰዎች ራሳቸው ከየት እንደመጡ ማግኘት አቅቶአቸዋል፤›› በማለት፣ ‹‹ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የማይቀበለው ርኩሰት ነው›› ብለው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወረራውን እንዲታገለው አሳስበዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር የተወከለ የአመራር አባል፣ ‹‹የምዕራባዊያን ረዥሙ እጅ ባህር ተሻግሮ እዚህ ደርሷል፡፡ ይህንን ዓይነት ቆሻሻ ባህል የሚሸከም ህሊና ግን የለንም፡፡ ጉዟችንን የሚያቀጭጭ ነቀርሳ ነው፡፡ በሕጋችንም ወንጀል ነው፤ በባህላችንም ነውር ነው፤›› ብሏል፡፡ ሌላ ወጣት ተናጋሪም፣ ምዕራባዊያን ኃጢአት ሥሩና ዕርዳታ እንስጣችሁ ከሆነ እያሉን ያለው፣ ‹‹በኃጢአት የመጣ ገንዘብ በአፍንጫችን ይውጣ›› የሚለውን ንግግሩ በከፍተኛ ጭብጨባና ተቀባይነት የታጀበ ነበር፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ወክለው የመጡ አንድ ተናጋሪም፣ የአውሮፓ ፓርላማ ኅብረት እንዲህ ዓይነቱን ጉዳይ በአጀንዳነት ለመነጋገር ብዙ ጊዜ ግፊት ማድረጉን ጠቅሰው፣ የአፍሪካ-ካሪቢያንና-ፓስፊክ ፓርላማ ኅብረት ግን መቃወሙን ገልጸው፣ ‹‹ከዕርዳታ ጋር የምታያይዙት መብት ከሆነ ዕርዳታችሁ በአፍንጫችን ይውጣ፣ አንፈልግም፤›› ብለናቸዋል የሚለውን የወጣቱን ንግግር ደግመው አረጋግጠዋል፡፡ ተሰብሳቢዎች የመንግሥት አቋም የሃይማኖት መሪዎች ያወጡት ጠንካራ አቋም መሆኑ አስደስቶአቸዋል፡፡ የፓርላማ አባሉም ከፍተኛ ጭብጨባ ተደርጎላቸዋል፡፡ ተሳታፊዎቹም በዚህ በኩል ለግብረሰዶም ያላቸውን ተቃውሞና ውግዘት ገልጸዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች፣ በመጨረሻ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ሁሉም በአቡነ ጳውሎስ የቀረበውን የአቋም መግለጫ ደግፈው፣ መንግሥት በውጭ ሰዎች በጉዲፈቻ በሚያድጉ ልጆች ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ፣ ድርጊቱን እንዲያወግዝና የተሳሳቱትንም መምከርና ማረም እንዳለበት፣ ሕዝቡም ከዚህ ወረራ ራሱን እንዲጠብቅ ጠይቀዋል፡፡
አንድ ስሙን ያልጠቀሰ ወጣት በዘመዱ በስድስት ዓመቱ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ከተፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ ለ20 ዓመታት ያህል ለግብረሰዶምነት መጋለጡን፣ አሁን ከኤችአይቪ/ኤድስ ጋር እንደሚኖር ገልጾ፣ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ አሁን ወደ ጤነኛ ሕይወቱ ለመመለስ በትግል ላይ መሆኑን ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ሌሎችም በተመሳሳይ ችግር የተጠቁ ኢትዮጵያዊያን ግብረሰዶማውያን የሚረዳቸው ካገኙ ከችግሩ ለመውጣት እንደሚፈልጉ ተናግሯል፡፡