ማውጫ፦ ምልከታ
“ቤተ ክርስቲያናችን አዲስ ፓትርያርክ ከመምረጧ አስቀድሞ አሁን ከገባችበት ዝብርቅርቅ ሁናቴ ለማገገም፣ ከሐዘኗም ለመጽናናት እና አሠራሯን በሥርዓተ አበው መሠረት ለማከናወን ጊዜ ያስፈልጋታል።”
(ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 11/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 17/ 2012/ READ THIS ARTICLE IN PDF)፦ ቅዱስ ፓትርያርኩ እነሆ አረፉ። በብዙ እሰጥ አገባዎች የተሞላው ዘመነ ፕትርክናቸው አሁን ሌላ እሰጥ አገባ ሊፈጥር እነሆ ተፈጠመ። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ በመስቀለኛ መንገድ ላይ እንደቆመች ናት። ይህንን የፕትርክና ምርጫ በሰላማዊና ክርስቲያናዊ መንገድ ማካሔድ ከቻለች ብሩህ ዘመን፣ አልያም ደግሞ በግርግር እና በጥቅመኞች ፍላጎት በሚመራ አሠራር ከተከናወነም ሌላ የመከራ ዘመን ሊጠብቃት ይችላል።
በአዲሱ ፓትርያርክ ምርጫ ላይ የራሳቸው “ጥቅም” እና ፍላጎት ያላቸው አካላት፣ ግለሰቦች እና ቡድኖች መኖራቸው እሙን ሲሆን ከነዚህ ሁሉ ኃይለኛው እና የረዥም ጊዜ ዕቅድ እና ሥልት ያለው ግን መንበረ መንግሥቱን የተቆናጠጠው የኢሕአዴግ አስተዳደር ነው። በበረሃ ወታደራዊውን መንግሥት ሲታገል ከነበረበት ዘመን ጀምሮ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ ስልት ነድፎ ሲንቀሳቀስ ከመቆየቱም በላይ በመንግሥትነት በቆየባቸው ዓመታትም ይህንኑ ቀጥሎ ሲያከናውን ቆይቷል። ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ ቢያንስ የ38 ዓመት ዕቅድና ተሞክሮ አለው ማለት ነው። 17 ዓመት በበረሃ፣ 21 ዓመት በመንግሥትነት።
ስለዚህም ከአቡነ ጳውሎስ ሕልፈት በኋላ ማን ሊተካ እንደሚችል ከማንም የበለጠ ቀድሞ እንደሚያስብ የታወቀ ነው። በርግጥም ይህንን ሐሳቡን አሁን በፍጥነት፣ በግርግር፣ በዚህ ሁሉ ትርምስ መካከል የሚያደርገው ከሆነ ቤተ ክርስቲያናችን ባለፉት 20 ዓመታት ካሳለፈችው አሳዛኝ ሁኔታ የበለጠ አዘቅት ውስጥ ልትወድቅ እንደምትችል ለመገመት የአቡነ ጳውሎስን ዘመን ማስታወስ ብቻ ይበቃል። የሚቀጥለው ጊዜ እንዲያውም ከእርሳቸው ዘመን የከፋና “ጳውሎስ ማረኝ” የሚያሰኝ ሊሆን ይችላል። በታሪክ እንደምናውቀው ከክፉ መሪዎች ሕልፈት በኋላ የሚመጡ መሪዎች የበለጠ ክፉ የሚሆኑበት ብዙ አጋጣሚ አለ። የቀዳማዊ አጼ ኃ/ሥላሴን ዘመን “አስከፊ ነው” ያለው ወታደራዊ መንግሥት “ጃንሆይ ማሩኝ” አሰኝቶን እንዳለፈው ማለት ነው።
የኢሕአዴግ ቤተ ክርስቲያንን የተመለከተው “ፖለቲካዊ ትንታኔ” ገና ከትግሉ ዘመን ጀምሮ ፈር በያዘ መልክ የተጠናና አቋም የተያዘበት እንደሆነ የህወሐት መሥራችአረጋዊ በርሄ ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ባደረጉት የምርምር ሥራቸው (A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilisation in Ethiopia/Amsterdam 2008) ላይ ጽፈውልናል። የፓርቲው ሃይማኖትን በተመለከተ የያዘው ይህ አቋም በተለይም ነባሮቹን የኢትዮጵያ ቤተ እምነቶች የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እና እስልምናን የተመለከተ መሆኑን፣ ኮሚኒስታዊ ፓርቲዎች ሁሉ ባላቸው “የጨቋኝ - ተጨቋኝ” ትንታኔ መሠረትም እነዚህ ሁለቱ ቤተ እምነቶች በተለያየ ጎራ እንዲቀመጡ መደረጋቸውን፣ ክርስትና ጨቋኝ፣ እስልምናም ተጨቋኝ ተብሎ መፈረጁን አንብበናል።
ዶ/ር አረጋዊ ባብራሩት የኢሕአዴግ ትንታኔ መሠረት “ቤተ ክርስቲያን ከቀድሞቹ መንግሥታት ጋር “በነበራት ቁርኝት” ከገዢው መደብ ጋር የተሰናሰለ የጥቅም እና የጨቋኝነት ግንኙነት ነበራት። በነዚህ ረዥም የጭቆና ዓመታት ከተጨቆኑት መካከል ደግሞ ሙስሊሞች” ይገኙበታል፤ ስለዚህም ኢሕአዴግ ይኼንን የጭቆና ቀንበር “ለመስበር” እና እኩልነትን ለማስፈን የተከተለው ፖሊሲ፣ “ቤተ ክርስቲያንን ማምከን/ፍሬ ቢስ ማድረግ” እና “ሙስሊሞችን ማንቀሳቀስ” ("neutralizing the Church and Mobilizing Muslims) ነው። (ገጽ. 300)
እንደ ዶ/ር አረጋዊ ገለጻ ከሆነ “በኢህአዴግ እና በቤተ ክርስቲያን መካከል የነበረው ግንኙነትከመጀመሪያው ጀምሮም ችግር ያልተለየው” ነበር። የትግሉ ማዕከል ከነበረው ከትግራይ ስንነሣ በሕዝቡ መካከል የሚደረገው ማንኛውም ግንኙነት በቤተ ክርስቲያኒቱ እና በአገልጋይ ካህናቷ ቁጥጥር ሥር የወደቀ ነው። ሰርጉ፣ ክርስትናው (የሕጻናት ጥምቀቱ)፣ ቀብሩ እና በጎረቤቶች አለመግባባት ወቅት ያለው ሽምግልናውና እርቁ በሙሉ የሚፈጸመው በቤተ ክርስቲያን በኩል ነው። ያንንም ለማከናወን ደግሞ በቂ ካህናት አሉ። በተጨማሪም እያንዳንዱ ቤተሰብ ሕይወቱን የሚከታተሉ አባቶች (የነፍስ አባቶች) በነፍስ ወከፍ አለው። ስለዚህም በያንዳንዱ አካባቢ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሕዝቡ ሕይወት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት አላት።
በሁለተኛ ደረጃ ቤተ ክርስቲያን በሕዝቡ እና በመንግሥታት መካከል ድልድይ ሆና ትሠራለች። ዶ/ር አረጋዊ እንዳሉት “ቤተ ክርስቲያኒቱ ሁልጊዜም ካለፉት ነገሥታት ጋር አብራ ቆማለች፤ መንግሥታቱም ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትኖር፣ እንድትስፋፋ እና አንድነቷ እንዲጠበቅ” ረድተዋታል። ቤተ ክርስቲያን ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ አገር አቀፍ ድረስ ተቋሟን ከመዘርጋቷም በላይ በመንግሥትና በተቀናቃኞች መካከል ለሚፈጠር ቅራኔ በአስታራቂነት እስከመግባት ትደርሳለች። ምእመናኗም ለመንግሥታቸው እንዲገዙ ታስተምራለች፣ አገራዊ ብሔርተኝነት እንዲዳብርም በማዕከልነት አገልግላለች። ባንዲራን የመሳሰሉ አገራዊ ምልክቶችን በበዓላቷ ሳይቀር ከፍ አድርጋ በማውለብለብ ብሔራዊ ማንነትን (national consciousness) ገንብታለች። የቤተ ክርስቲያን በዓላት ካለ ሰንደቅ ዓላማ በጭራሽ አለመከበራቸውን ልብ ይሏል።
በሦስተኛ ደረጃ በየዘመኑ የነገሡ ነገሥታት በቤተ ክርስቲያን እስካልተቀቡ ድረስ ንግሥናቸው ተቀባይነት አልነበረውም። ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን የነገሥታቱ ሥልጣን አረጋጋጭ እና ወሳኝ ሆና አገልግላለች። በአኩሱም ጽዮን ለሚፈጸመው ለዚህ ቅብዓ መንግሥት ነገሥታቱ በበኩላቸው ርስት እና ጉልት በመሥጠት ቤተ ክርስቲያኒቱን ጠቅመዋል። አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሳይቀሩ መተዳደሪያ እንዲኖራቸው፣ የአጥቢያው ምእመንም እንዲንከባበከባቸው፣ አገልጋይ ካህናቱም የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዲያገኙ የአጼዎቹ አስተዳደር ጠቅሟቸዋል።
“አጼያዊው አስተዳደር ከወደቀና ቤተ ክርስቲያን ርስት ጉልቷን ሁሉ ካጣች በኋላ በወታደራዊው መንግሥት እና በሰሜን በሚዋጉ ተቃዋሚዎች መካከል አጣብቂኝ ውስጥ ገባች” ይላሉ አረጋዊ በርኸ። “ኢ.ዲ.ዩን በመሳሰሉ ፓርቲዎች ላይ ተስፋ አሳድራ ብትቆይም ሳይሳካ” ቀርቷል።
እንደ ዶ/ር አረጋዊ በርኸ ገለጻ ከአብዮቱ በኋላ የትግራይ ሕዝቦች ነጻ አውጪ ግንባር (ሕወሐት) ቤተ ክርስቲያን በሕዝቡ መካከል ያላትን ሚና እና አብዮቱን ከሚቃወሙ ኃይሎች ጋር ሊኖራት የሚችለውን ግንኙነት ተረዳ። ግንባሩ በሚያደርገው ትግል ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ከመንገዱ ላይ እንደተደነቀረች እና በጥንቃቄ ሊይዛት እንደሚገባ አወቀ። ቤተ ክርስቲያኒቱን የትግሉ አካል እና ደጋፊ ማድረግ እንደሚገባው ተገነዘበ። ስለዚህም ሊያዳክሟትና እና ለዓላማው መሳካት እንድትቆም ሊያደርጉ የሚችሉ ተከታታይ ሥራዎችን ሠራ - ይላሉ።
ግንባሩ በመጀመሪያ የወሰደው ርምጃ ወታደራዊው መንግሥት ያወጀውን “የመሬት ላራሹ” አዋጅ ባለመቀልበስ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብቷ፣ ንብረቷ፣ መሬቷ እንዳይመለስላት ማድረግ፣ በዚህም ጉልበቷን ማዳከም እና ለሺዎች ዓመታት የነበራትን አቅም በመስበር ከአማኞቿ ጋር አዲስ ውል እና ቃል ኪዳን እንድትገባ ማስገደድ (በምእመናን ምጽዋት ላይ እንድትደገፍ ማድረግ)፣ ልትረዳቸው የምትችላቸውን የተቃውሞ ኃይሎች እንዳትረዳ ደካማ ማድረግ ነው። ቤተ ክርስቲያን የነበራትን መሬት ራሱ ፓርቲው በመውረስ ለሕዝቡ ለማከፋፈል ከመሞከሩም በላይ የቤተ ክርስቲያንን መሬት ለመጠቀምና ለማከፋፈል ፍላጎት በሌለባቸው አካባቢዎችም ፓርቲው ራሱ በመቆጣጠር ተሰሚነቱን ከፍ ለማድረጊያነት ተጠቀመበት።
የቤተ ክርስቲያኒቱን ተጽዕኖ በማዳከሙ በኩል ፓርቲው በሁለተኛ ደረጃ የወሰደው ርምጃበማንኛውም የዕለት ተዕለት ግንኙነቱ ማለትም (ሰርጉ፣ ክርስትናው (የሕጻናት ጥምቀቱ)፣ ቀብሩ እና በጎረቤቶች አለመግባባት ወቅት ያለው ሽምግልናውና እርቁ) ሕዝቡ ዓይኑን ከቤተ ክርስቲያን ላይ እንዲያነሣ እና ፓርቲው በሚያቋቁማቸው ተቋማት ላይ እንዲያደርግ በዚህም ቤተ ክርስቲያን አስፈላጊነቷ ዝቅ እንዲል ማድረግ ነው። እንደታሰበውም ቤተ ክርስቲያን የሸምጋይነት ተግባሯን እንዲሁም ቦታዋን አጣች።
በሦስተኛ ደረጃ ፓርቲው ያደረገው ነገር ተከታታይ ሴሚናሮችን ለተመረጡ ካህናት ማካሔድ ነበር። ይህ እ.ኤ.አ በ1979 የተካሔደው ሴሚናር ዓላማ በትግራይ ያለችውን ቤተ ክርስቲያን ከመላው አገሪቱ ካለው መዋቅራዊ አሠራር በመለየት እና በመነጠል፣ የትግራይ ብሔርተኝነትን በማጠናከር ፓርቲው ለተነሣለት ዓላማ እንዲጠቅሙ ማድረግ ነው። የቤተ ክርስቲያኒቱን ተጽዕኖ ለመቋቋም ትግራዋይነትን እና የትግራይ ብሔርተኝነትን መቀስቀሱና ማራገቡ ትልቅ አስተዋጽዖ ሊያደርግ ቻለ። በወረዳ ደረጃ የነበረው የትግራይ ካህናት ተከታታይ ሴሚናር የተከናወነው “በአንደበተ ርቱዑ የቲዮሎጂ ምሩቅ በገብረ ኪዳን ደስታ” ሲሆን የውይይቱ ርዕሰ ጉዳይም የኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን አስተዳደርን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ድርጅትን ዓላማ በተቀበሉ እና “ትግራዋይነትን እና የትግራይ ግዛትን በሚያስፋፉ ካህናት” መተካት ነበር።
ይህ እንቅስቃሴ “የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ካህናትን እና ተርታ ምእመናንን በማንቀሳቀስ እና በማነቃቃት” የተከናወነ ሲሆን ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስተዳደር በመነጠል እና በመገንጠል፣ ዋናዋን እናት ቤተ ክርስቲያን በማዳከም ላይ ያተኮረ ነበር። በአቶ ስብሐት ነጋ የሚመራ የስለላ መዋቅር የተደራጀ ሲሆን የፓርቲውን ሰላዮች በመነኮሳት እና በካህናት ስም ደብረ ዳሞን በመሳሰሉ ዋና ዋና ገዳማት በማስገባት እና ቤተ ክርስቲያኒቱን በመቆጣጠር ላይ ሥራ ተሠርቷል። እ.አ.አ በ1979 የተጀመረው የካህናት ተከታታይ ሴሚናር አድጎ በ1987 እና በ1989 ክልላዊ እና አገር አቀፋዊ የካህናት ጉባኤዎች ‘ነጻ በወጡ መሬቶች ላይ” ሊካሔዱ ችለዋል። ዓላማውም የቲ.ፒ.ኤል.ኤፍን ዓላማ የተቀበለች ቤተ ክርስቲያን በትግራይ መመሥረት ነበር። በውጤቱም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ልትከፈል ችላለች፣ አንደኛው በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፤ ሌላኛውና ሁለተኛው ደግሞ በፓርቲው ሥር ያለ አስተዳደር። ሁለቱም አስተዳደሮች ፓርቲው መቐለን እስከተቆጣጠረበት እስከ 1990 ድረስ በትግራይ ውስጥ በትይዩ ሲሠሩ ቆዩ። መቐለ “ነጻ ሲወጣ” አንደኛው አስተዳደር አበቃለት፣ በፓርቲው አስተዳደር ተተካ ሲሉ ያትታሉ።
በ1983 ዓ.ም ግንቦት ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር በወታደራዊው መንግሥት ጸረ እምነት አቋም እና በአጠቃላይ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ የተነዋወጸው ቤተ ክህነት ተከፋፍሎ ለበለጠ መለያየት ተመቻችቶ ነው የቆየው። በኢሠፓነት የተከሰሱት ብፁዕ ወቅዱስ አበኑነ መርቆርዮስ “በፈቃዳቸው” መንበራቸውን ለቅቀው ብፁዕ አቡነ ዜማ ማርቆስ “ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ” ሆነው ተመረጡ። በአንድ ጽሑፋችን እንዳልነው በዘረኝነት በሽታ በጽኑዕ የታመመው ቤተ ክህነት በሌላ የዘረኝነት ወረርሽኝ ተመታ። በአንድ ጽሑፋችን እንዳልነው፦ “የጎንደር ምንቸት ወጣ፣ የትግሬ ምንቸት ገባ”። ዘረኝነቱ ቀጠለ። መንግሥትም ቀጥተኛም ቀጥተኛ ባልሆነም መንገድ ቤተ ክህነቱን ይዘውረው ገባ።
ቤተ ክህነቱ በየትኛው ዘመን ፍፁማዊ ነጻነት ነበረው ለማለት ባይቻልም እንደ አሁኑ ደግሞ “ዳዊት ባልደገመ አፋቸው፣ አቡነ ዘበሰማያት በማያውቅ አንደበታቸው” ቤተ ክህነቱን እንወክላለን የሚሉ፣ በእምነታቸው ኢ-ኦርቶዶክሳዊነት የሚታወቁ፣ በገንዘብ ዘረፋ የተሰማሩ፣ በይፋ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባርን እና ኢትዮጵያዊ ባህልን የሚያጎድፉ ሰዎች ተሰግስገውበት አያውቁም። ይህ 20 ዓመት ሥርዓተ ምንኩስና፣ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፣ አሠረ ክህነት፣ ፕትርክና እና የተከበረ አባትነት፣ በአንድ አፍ ሁለት ምላስ አለመሆን ወዘተ የተንኮታኮተበት ዘመን ነው።
በአጠቃላይ በዚህ ሁሉ ግርግር መካከል፣ ባልተረጋጋ መንፈስ፣ ጤነኛው ከቀማኛው፣ እውነተኛ እረኛው ከነጣቂው ባልተለየበት እና ትክክለኛ ክርስቲያናዊ አገልግሎት ለመስጠት ቤተ ክህነቱ መዋቅራዊ ጤንነቱ ባልተጠበቀበት ሁኔታ፣ ሕግጋቱ እና አሠራሮቹ ሳይስተካከሉ፣ ቅዱስ ሲኖዶስም የማይነቃነቅ ሉዓላዊ የበላይነቱን እንደገና ከእጁ ሳያስገባ አዲስ ፓትርያርክ መምረጥ ከዘመነ አቡነ ጳውሎስ ለባሰ ችግር ሊያጋልጠን ይችላል።
በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 13፡5 ላይ እንደተጠቀሰው በፓትርያርክ ምርጫ ላይ የሚሳተፉት “የቅዱስሲኖዶስ አባላት በሙሉ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይሥራ አስኪያጅ፣ የየመምሪያና ድርጅት ሓላፊዎች፣ የጥንታውያን ገዳማት አበምኔቶች የአድባራትአስተዳዳሪዎች ከየሀገረ ስብከቱ ሰበካ ጉባኤያት በዕድሜ ከሠላሳ ዓመት ያላነሱ የካህናትና የምእመናንተወካዮች እንዲሁም ዕድሜያቸው ከ22 አስከ 30 ዓመት የሆኑ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮችሲሆኑ በጠቅላላው በሰበካ ጉባኤው የሚወከሉት ከአንድ ሀገረ ስብከት አሥራ ሁለት ሆነውበሥጋወደሙ የተወሰኑ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የጸኑ መሆን አለባቸው” ይላል።
በዚህ መሠረት ባለፉት ዓመታት በተለያየ ምክንያት በየአብያተ ክርስቲያናቱ ላይ የተሾሙ፣ በምግባራቸውም በእምነታቸውም አስነቃፊነት በተለያዩ ጊዜያት የምዕመናን ቅሬታ፣ ዕንባና ሐዘን የወረደባቸው ሰዎች ዞረው “ፓትርያርክ መራጮች” ሆነው ይመጣሉ ማለት ነው። በርግጥ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ “የምርጫው አፈጻጸም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ይሆናል” ቢልም አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ውጤቱ ሳይታለም የተፈታ ነው።
የምዕመናን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን ውክልናም በተመለከተ ምዕመናን እና ወጣቶቹ በቅጡ ሊመክሩበት ይገባል። የምንመርጠው ፓትርያርክ እንጂ የቀበሌ ሊቀ መንበር አይደለም። ከየአህጉረ ስብከቱ የሚወከሉ ሰዎች በቢሮ-ለቢሮ የደብዳቤ ልውውጥ እና በድርጅታዊ አሠራር የሚላኩ መሆን የለባቸውም። ለዚህም በየአብያተ ክርስቲያናቱ ያሉ ኦርቶዶክሳውያን ኃላፊነት አለባቸው።
ከዚህ አንጻር ቤተ ክርስቲያናችን አዲስ ፓትርያርክ ከመምረጧ አስቀድሞ አሁን ከገባችበት ዝብርቅርቅ ሁናቴ ለማገገም፣ ከሐዘኗም ለመጽናናት እና አሠራሯን በሥርዓተ አበው መሠረት ለማከናወን ጊዜ ያስፈልጋታል። ከ40 እስከ 80 ቀናት በቂ አይደሉም። አሳማኝም አይሆንም። ቅ/ሲኖዶስ የምርጫ ደንብ ለማውጣት ጊዜ ያስፈልገዋል እንላለን። ጊዜ፣ ጊዜ፣ ጊዜ። መመሪያ፣ መመሪያ፣ መመሪያ። ደንብ፣ ደንብ፣ ደንብ። መንግሥትም አጁን ሰብሰብ ሊያደርግ ይገባዋል። ብፁዓን አባቶችም ኃላፊነታቸውን በቅጡ መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
ቸር ወሬ ያሰማን፤
አሜን፡፡
No comments:
Post a Comment